ግብጽ የ2019 አፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ሀገር ሆና ተመረጠች

1594

ታህሳስ 30/2011 የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ግብጽን የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ሀገር አድርጎ መርጧል፡፡

ካፍ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ 24 ብሄራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበትን የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ሀገርን በነገው እለት እንደሚያሳውቅ ገልጾ የነበረ ቢሆንም ቀኑን ለምን ዛሬ እንዳደገረው የገለፀው ነገር የለም፡፡

ደቡብ አፍሪካ እና ግብጽ ውድድሩን ለማስተናገድ እስካሁን ለካፍ ይፋዊ ጥያቄ ያቀረቡ ሀገራት የነበሩ ሲሆን ካፍ ዛሬ ባደረገው ምርጫ ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር በታሪኳ ለአምስተኛ ጊዜ ትልቁን ውድድር እንድታስተናግድ መርጧታል፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሽን ካሜሩንን የ2019 አፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጅ አድርጎ የመረጠ ቢሆንም ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ውድድሩን ለማስተናገድ የሚያስችል በቂ ግዝጅት ባለማድረጓ ተቀምታለች፡፡

ዛሬ የአፍሪካ ዋንጫው አዘጋጅ ሆና የተመረጠችው ግብፅ ለውድድሩ በስድስት ወራት ውስጥ መዘጋጀት ይኖርበታል ተብሏል፡፡

የ2019 አፍሪካ ዋንጫ እኤአ ከሰኔ 15 እስከ ሀምሌ 13 ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የውድድሩ አዘጋጅ ሀገር እና የአፍሪካ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትም የዛሬው የዝግጅት አንዱ አካል ሲሆን የግብፁ ሞሀመድ ሳላ በድጋሚ የማሸነፍ እድሉ ሰፊ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ምንጭ፡ ቢቢሲ ስፖርት