6ኛ ዙር አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ታህሳስ 30/2011 6ኛው ዙር አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት በመጪው ሐሙስ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ገለጸ።

ድርጅቱ አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ስነ-ስርዓቱን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት እስካሁን ድረስ ለ5ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን ዘንድሮም ለ6ኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራቱ እንደገለጹት፤ የሽልማቱ ዓላማ በአገሪቷ ያሉ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች እንዲሁም በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ለጥራት የሚያደርጉትን ስራ በማበረታታት እውቅናና ሽልማት እንዲያገኙ ማድረግ ነው።

በጥራት ጽንሰ ሃሳብና ትግበራ ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላትና ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህም የአገሪቷ ተቋማትና ድርጅቶች ዓለም ከደረሰበት የጥራት ደረጃ አኳያ ራሳቸውን እንዲፈትሹ ለማድረግም እድል የሚፈጥርና ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራትም ጉልህ ሚና ያለው ነው ብለዋል።

እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ በአገራችን የጥራትና ተወዳዳሪነት አስፈላጊነት እስካሁን በሚፈለገው መጠን ግንዛቤ ባለመያዙ ምክንያት የሚፈለገውን ያህል ተወዳዳሪ ማግኘት አልተቻለም።

በዚህ ዓመት 330 ለሚሆኑ ድርጅቶች እንዲወዳደሩ ጥሪ የተደረገ ቢሆንም ፍቃደኛ የሆኑትና እስከ መጨረሻው የዘለቁት 40ዎቹ ብቻ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ከተሳተፉ 40 ድርጅቶችና ተቋማት መካከል በአምራች ዘርፍ፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በጤና ተቋማትና በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው።

እስካሁን ከ1ኛ እስከ 5ኛ ዙር በተካሄደው የጥራት ሽልማት 49 ተቋማት የአንደኛ ደረጃ የልዕቀት ማዕረግ ተሸላሚዎች መሆን የቻሉ ሲሆን በዘንድሮ የ6ኛ ዙር ሽልማት 9 ተቋማት የአንደኛ ደረጃ ተሸላሚዎች እንደሚሆኑ ተገልጿል ።

አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ስነ-ስርዓቱ በመጪው ሐሙስ ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና አመራሮች እንዲሁም አምባሳደሮች በተገኙበት ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም