በጎንደር ከተማ የማምረቻና የመሸጫ ሼዶች በህገ ወጥ መንገድ ለሦስተኛ ወገን እየተላለፉ ነው....የከተማው ወጣቶች

82

ጎንደር ታህሳስ 30/2011 በጎንደር ከተማ ለወጣቶች የተዘጋጁ የማምረቻና የመሸጫ ሼዶች በህገ ወጥ መንገድ ለሦስተኛ ወገን በኪራይ እየተላለፉ ነው ሲሉ ወጣቶቹ ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡

ወጣቶቹ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ባለማግኘታቸው ወደሥራ መግባት እንዳልቻሉም ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ  ወጣቶች መካከል ወጣት ገብረማርያም ድረስ እንዳለው በከተማው በተገነቡ ሼዶች የገቡ በርካታ አንቀሳቃሾች ሥራ ሳይጀምሩ ሼዶችን ለበርካታ ዓመታት ዘግተው አስቀምጠዋል።

አንዳንዶቹም ለሌላ አካል አከራይተውና ቁልፍ በመሸጥ የግል መጠቀሚያ ማድረጋቸውን ነው የገለጹት።

በዶሮ እርባታ ለመሰማራት የቦታ ጥያቄ ካቀረበ ከአንድ ዓመት በላይ ቢሆነውም እስካሁን ድረስ ቦታ ማግኘት እንዳልቻለ ወጣት ገብረማርያም ተናግሯል፡፡

"የከተማው አስተዳደር ተከታትሎ እርምጃ አለመወሰዱ ህገ-ወጥነትን የሚያበረታታ ነው" ሲልም ቅሬታውን ገልጿል፡፡

በዳቦ መጋገር የሥራ ዘርፍለመሰማራት የቦታ ጥያቄ ካቀረበ ስድስት ወር እንደሞላው የተናገረው ደግሞ የማራኪ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሺመልስ አስናቀው ነው፡፡

"እኔና ሌሎች ወጣቶች ሰርተን ለመለወጥ የቦታ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ አልተሰጠንም፤ ግለሰቦች ሼዶችን ያለሥራ ዘግተው በማስቀመጥና ለሌላ በማከራየት የሚፈጽሙት ህገ-ወጥ ተግባር ሊታረም ይገባል" ብሏል፡፡

ሌላው የከተማው ነዋሪ አይናለም አሰፋ በበኩሉ እንዳለው የማምረቻና የመሸጫ ሼዶችን የተረከቡ ህገ-ወጦች በወር ከ1 ሺህ ብር እስከ 2ሺህ ብር ድረስ በማከራየት የሌሎች ሥራአጥ ወጣቶችን እድል እየዘጉ ይገኛሉ፡፡

በማራኪ ክፍለ ከተማ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት የአንድ ማዕከል ተወካይ ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ መስከረም ካሳው በክፍለ ከተማው የሚገኙ ሼዶችን ለኢንተርፕራይዞች የሚያስተላልፈው የከተማ አስተዳደሩ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

በክፍለ ከተማው ሥራ ያልጀመሩ ኢንተርፕራይዞችን በጥናት በመለየት በአዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ ስራእጥ ወጣቶች ተላልፈው እየተሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ኢንተርፕራይዞች ሼዶችን በኪራይ ለሦስተኛ ወገን በማስተላለፍ ላልተገባ አላማ እያዋሉ ናቸው በሚል የሚደርሱ ጥቆማዎችን ክፍለ ከተማው እያጣራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ የተቋማት ግንባታና ቁሳዊ አቅርቦት ቡድን መሪ አቶ ታደሰ አባይ ለአዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ሼዶች የሚተላለፉት በአሰራርና መመሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

"ሥራ ፈላጊዎቹ በሚያቀርቡት ማመልከቻና የጊዜ ቅደም ተከተል እንዲሁም የሚሰማሩበትን ዘርፍ መሰረት በማድረግ ወጣቶቹ በሼዶቹ ገብተው እንዲሰሩ ይደረጋል" ብለዋል፡፡

በቅርቡም ከአረብ አገራት የተመለሱና በሚሰሩበት የሥራ ዘርፍ የተለያዩ ስልጠናዎችን የወሰዱ ሥራ ፈላጊዎችም የእድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"ሼዶችን ተቀብለው ወደ ሥራ ያልገቡ ኢንተርፕራይዞች ነበሩ" ያሉት ቡድን መሪው የአንድ ወር የማስጠንቀቂያ ጊዜ ተሰጥቷቸው ሥራ ያልጀመሩ 12 ኢንተርፕራይዞችን ሼድ በመንጠቅ ለአዲስ ኢንተርፕራይዞች መሰጠቱን ገልፀዋል።

በመንግስት በኩል የመብራትና የውሃ አቅርቦት ያልተሟላቸው ሼዶችን ተረክበው የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች ወደሥራ እንዲገቡ መሰረተ ልማት እንዲሟላ ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ መቅረቡንም አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ 52 ሼዶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን 250 ኢንተርፕራይዞችም ቦታ ተረክበው በመስራት ላይ እንደሚገኙ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የማምረቻና የመሸጫ ሼዶችን ቁጥር በመጨመር ተጠቃሚ ኢንተርፕራይዞችን ለማሳደግም በከተማ አስተዳደሩ በኩል ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ በቅድመ ግንባታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም