ፓርቲው ትውውቅ አካሄደ

595

ሰመራ ታህሳስ 29/2011 የአፋር ህዝብ ፓርቲ እራሱን ለማስተዋወቅ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ  በሰመራ ከተማ ተካሄደ፡፡

በውይይት መድረኩ  የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ  ፓርቲ  (አብዴፓ) ለፓርቲው ድጋፉን ገልጿል፡፡

የአፋር ህዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ኮንቴ ሙሳ ትናንት በተካሄደው መድረክ  እንዳሉት የአፋር ህዝብ ሰፊ የሆነ ለም መሬትጨምሮ ልዩ ልዩ የተፈጥሮ ሃብት ቢኖረው  በተገቢ ሊጠቀም ባለመቻሉ በድህነት ውስጥ ይገኛል፡፡

ለዚህም ምክንያቱ ሀቀኛ የህዝብ አገልጋይ ባለመኖሩ እንደሆነ ጠቅሰው ፓርቲው ይህንን በደል ውጪ ሆኖ  ሲያሰማ እንደነበረና በሀገሪቱ  በተፈጠው ለውጥ ወደ ሀገሩ ገብቶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የመጣው የስልጣን ጥማት ኖሮት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

የትግላቸው መነሻ በክልሉ ህዝብ ላይ ሲደርስ የነበሩ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች ለማስቆም እንዲሁም ጥቅሙ ለማስከበር መሆኑን የፓርቲ ሊቀመንበር ገልጸዋል፡፡ 

በሀገሪቱም ሆነ በክልሉ  የተጀመረው ለውጥ የነበረውን  አስከፊ የጭቆና ዘመን አብቅቶ ምቹ መደላድል መፈጠሩን አውስተው ” በዚህም ዛሬ አፋር በራሳችን ልጆች ልማቷና እድገቷ የሚፋጠንብት ትክክለኛ ጊዜ ላይ እንገኛለን” ብለዋል

ፓርቲው በቀጣይ የአፋር ህዝብ ከተደቀነበት ከፋፋይ የጎሰኝነት አመለካከት በመላቀቅ ያሉትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች አልምቶ በፍትሃዊነት ተጠቃሚ  እንዲሆን የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን መቅረጹን ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የክልሉን መንግስት የሚመራው የአብዴፓ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጠሃ አህመድ ፓርቲያቸው የአፋር ህዝብን ማዕከል ያደረገ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት  በመገንባት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚተጋ ገልጸዋል፡፡

አቶ ጠሃ እንዳሉት በክልሉ ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ መፈጠር ለአፋር ህዝብ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዎ ፓርቲ መረጋገጥ ከሚኖረው ፋይዳ ባለፈ አብዴፓ  ለተሻለ ለውጥ  ነቅቶ እንዲሰራ ያደርገዋል፡፡

ከዚህ በፊት በመንግስትና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የነበረውን የጥላቻና  የመጠላላፍ ፖለቲካ አብቅቶ በመደጋገፍ ለህዝባቸው ልማትና ዴሞክረሲያዊ ሰርዓትን ግንባታ ተቀራርበው እንደሚሰሩም አስታውቀዋል፡፡

የአፋር ህዝብ ፓርቲ በክልሉ ለሚያደርጋቸው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

ከውይይት መድረኩ በኋላ የአፋር ህዝብ ፓርቲ የሰመራ ቢሮው ተመርቆ ተከፍቷል፤ በክልሉ  ዞኖችና ወረዳዎች  ቅርንጫፎች  እንደሚኖሩት ተገልጿል፡፡