የመንገዱ መከፈት የኤርትራና ኢትዮጵያ ህዝቦች ግንኙነትን ያጠናክራል– ነዋሪዎች

1065

ሁመራ ታህሳስ 29/2011 የሁመራ ኦምነሐጀር መንገድ  መከፈት  የኤርትራና ኢትዮጵያ  ወንድማማች ህዝቦች ግንኙነት  እንደሚያጠናክር በአካባቢው የሁለቱ ሀገራት ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ለ20 ዓመታት ተዘገቶ የቆየው የኢትዮ ኤርትራ አዋሳኝ የሁመራ ኦምነሓጀር መንገድ ዛሬ ተከፍቷል፡፡

መንገዱ ሲከፈት በነበረው ስነስርዓት ወቅት የሰቲት ሁሞራ ከተማ ነዋሪ አቶ ስዩም ኪዳነ  በሰጡት አስተያየት ” እኛ ወንድማማች ህዝቦች ነን፤ ዛሬ መንገዱ ክፍት መሆኑ የሁለቱም ህዝቦች  ትስስር እንዲኖር የላቀ ሚና አለው”ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር  በሁለቱ ህዝቦች መካከል የጠበቀ ግንኙነትና ዘላቂ የሆነ  ሰላም እንዲኖር የሚፈልጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ሌላው የሰቲት ሁመራ ነዋሪ አቶ ገብረ መስቀል ብርሃነ በበኩላቸው የሁመራ ኦምነሓጀር መንገድ መከፈት የኤርትራና ኢትዮጵያ ህዝቦች ግንኙነት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በዘላቂነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎታቸው መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የኦምነሐጀር ከተማ ነዋሪ አቶ ተስፋሚኪኤል የማነ በበኩላቸው ” የኤርትራ ህዝብ ሰላም ይፈልጋል፤  ከሰቲት ሁመራ ነዋሪዎች ጋር የገናን በዓል   ስናከብር በጣም ደስ ብሎኛል” ብለዋል፡፡

የተጀመረው ግንኙነት  ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚፈልጉ መሆናቸውን አመልክተው ለዚህም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናገረዋል፡፡ 

ሌላው የኦምነሓጀር ከተማ  ነዋሪ አቶ ዑስማን የሱፍ እንዳሉት የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች ግንኙነትና ሰላም  ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጠል ማድረግ ይገባል፡፡ 

የሁመራ ኦምነሓጀር መንገድ መከፈት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሮችን እንዲጎብት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው  ግንኙነቱ ዘላቂ እንዲሆን አጥብቀው እንደሚፈልጉም ተናግረዋል፡፡

የሁመራ ኦምነሓጀር መንገድ  ዛሬ ሲከፈት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ተገኝተዋል፡፡

የትግራይ ክልል ምክትል  ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድረ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዲሁም  የሁለቱም ከተሞች አስተዳዳሪዎችና ከከተሞቹ የማህበረሰብ ተወካዮችም ተገኝተዋል፡፡