በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ የነበሩ የጦር መሳሪያዎች ተያዙ

75
መተማ ግንቦት 18/2010 በተለያዩ ቀናት በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ የነበሩ የጦር መሳሪያዎች መያዛቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊና የኮማንድ ፖስት አባል ኢንስፔክተር አብራራው የኋላ ለኢዜአ እንደገለጹት በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች በመተማ በኩል ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ሲሞከር በቁጥጥር ስር የዋሉት የጦር መሳሪያዎች 58 ክላሽ እንኮቭ፣ ሽጉጥና በርካታ ጥይቶች ናቸው። ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎቹ በፀጥታ አካላትና በመከላከያ ሠራዊት አባላት ቅንጅታዊ ክትትል ግንቦት 12 ቀን 2010 ዓ.ም ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት በመተማ ወረዳ ደለሎ ቀበሌ ልዩ ቦታው በረከተ ኑሪ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ መያዛቸውን አስታውቀዋል። በዕለቱ 33 ክላሽ እንኮቭ ጠብመንጃ  ሦስት ሺህ 970 ጥይቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡ መሳሪያዎቹና ጥይቶቹን በትራክተር ተጭኖ ለመስገባት የሞከሩ ሁለት አዘዋዋሪዎች በሕግ ጥላ ስር መዋላቸውንና ሦስተኛው ተጠርጣሪ ማንነቱን በመለየት ክትትል እየተደረገበት መሆኑን ኢንስፔክተር አብራራው አስታውቀዋል። ሌሎች በወንጀሉ የተሳተፉ አካላት እንዳሉም የተደረሰበት መሆኑን አመልክተው እነሱንም ለመያዝ ከፍተኛ ክትትል እንደሚደረግም ገልፀዋል፡፡ በተመሳሳይ ግንቦት 13ቀን 2010 ዓ.ም በመተማ ዮሐንስ ከተማ በመንገድ ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ በአንድ ኤፍ ኤስ አር አይሱዚ የጭነት መኪና ውስጥ 25 ሽጉጦች ከ384 ጥይቶች ጋር ለመያዝ መቻሉን ኢንስፔክተር አብራራው አስታውቀዋል፡፡ በቀጠናው ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ መኖሩን ገልፀው፣ ይህን ለመከላከል ከሕብረተሰቡ ጋር በመሆን ጥብቅ የቁጥጥር እና የክትትል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል። ከሱዳን ጋር በሚያዋስኑ ዋና ዋና መተላለፊያ በሮችም ጥናትንና መረጃን መሰረት ያደረገና የፀጥታ አካሉና ሕብረተሰቡ በቅንጅት ቁጥጥር እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል። በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የሚሳተፉ ወንጀለኞችን በማጋለጥና ጥቆማ በመስጠት የአካባቢው ነዋሪ የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም