የምሽት የስርቆት ወንጀል በጅግጅጋ ከተማ እየተበራከተ ነው.....ነዋሪዎች

69

ጅግጅጋ ታህሳስ 28/2011  በጅግጅጋ ከተማ በምሽት መኖሪያ ቤቶችን በመስበር የሚፈጸም የተደራጅ የስርቆት ወንጀል እየተበራከተ መምጣቱን ነዋሪዎች ገለጹ።

በከተማው ቀበሌ 05 የሚኖሩት ሐጂ አህመድ መሐመድ እንዳሉት በመኖሪያ አካባቢያቸው ጨለማን ተገን በማድረግ ዘረፋ የሚፈፀሙ ግለሰቦች አሉ።

በየጊዜው ቤታቸው የሚዘረፉ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱ የደህንነት ስጋት ላይ ስለጣላቸው የሚመለከተው የመንግስት አካል አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የቀበሌ 08 ነዋሪ ወይዘሮ አያን አብዲራህማን በበኩላቸው ዘራፊዎቹ ተመሳሳይ ቁልፍ ይዘው በመምጣት በመኖሪያ ቤታቸው አንድ ክፍል ውስጥ የነበረን ንብረት በሙሉ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

"ሌሊት ከልጆቼ ጋር መኝታ ክፍል ነበርን ጥዋት ስንነሳ የቤታችን በር ሳይሰበር በውስጡ የነበሩ የተለያዩ እቃዎች ተዘርፈው ተወስደዋል" ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የመንገድ መብራቶችን በማብራትና ፖሊስም በጨለማ ቦታዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ስጋታቸውን እንዲያስወግድላቸው ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር መሐመድ አሊ በበኩላቸው ነዋሪዎቹ ያነሱት የዘረፋ ወንጀል  ችግር ትክክል መሆኑን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ወንጀል ፈጻሚዎችን በህብረተሰቡ ትብብር የመያዝ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

ማረሚያ ቤት የነበሩ ግለሰቦች በምህረት አዋጁ ተጠቅመው ከማረሚያ ቤት ከተለቀቁ ቦኋላ አንዳንዶቹ ተመልሰው በዛው ወንጀል መሰማራታቸው በስርቆት ወንጀል የተሰማሩ ግለሰቦች እንዲበራከት ማድረጉንም ጠቁመዋል።

የከተማው ነዋሪዎች ከፖሊስ ጋር በመሆን ወንጀልን እንዲከላከልና በከተማው ያለውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ማህበረሰቡን የማወያየት ሥራ መጀመሩንም ኮሚሽነር መሐመድ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም