የገና ዛፍና ውድ ጌጣጌጦች ኃይማኖታዊ ምክንያት የላቸውም ፡-የሀይማኖት አባቶች

128

አዲስ አበባ ታህሳስ 28/2011 በዓልን ለማክበር ሰዎች ዝግጅት የሚጀምሩት ከሳምንት አስቀድሞ ነው። በማህበረሰባችን ዘንድ የሻጭና ገዥ ክርክሮች፣ የዶሮ፣ የበጉና የሰንጋው ገበያ ግርግሩ፣ የእጣኑ፣ የቅቤውና ቅመማቅመም ሽታው በተለይ በበዓላት ሰሞን ልዩ ድባብ የሚፈጥሩ ናቸው።

የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ወይም ገና ደግሞ ኃይማኖታዊ በዓል ቢሆንም አከባበሩና ባህላዊ ተግባራቱ ከአገር አገር ይለያያል።

ገና በአገራችን ለረጅም ዓመታት ኃይማኖታዊ ስርዓቶቹ ተጠብቀው ሲከበር ቢቆይም አሁን አሁን በበዓል የሚተከለው ሰው ሰራሽ ጽዱ፣ በተለያዩ ቀለማት የተዋቡ አብረቅራቂ መብራቶችና ለስጦታ የሚውል ወረቀቶች ተሽቆጥቁጦ ማየት ተለምዷል፤ የቀያይ ኮፍያዎች፣ አብረቅራቂ ቁሶችና ፊኛዎች ሽያጭ ደግሞ አዲስ የንግድ መስክ ፈጥረዋል።

ፒያሳ ከወትሮዋ ለየት ባለ መልኩ በሰው ሰራሽ የብርሃን ቀለማት ተውባለች፤ በዚያ ግርግር መሃል ቀልብን ወደሚስቡ ዕቃዎች የሚያማትሩ በርካታ ገዥዎችም ይተራመሳሉ።

ሸማቾች ስለሚገዙት ዕቃና በዓሉ ላይ ስለሚያከናወኑት በርካታ ልማዶች ከእየሱስ ክርስቶስ ልደት ጋር እንዴት ሊያያዙ እንደቻሉ ጥያቄን ይፈጥራል።

ገና የእየሱስ ክርስቶስ ልደት የሚከበርበት ክርስቲያናዊ በዓል እንደሆነ ይታወቃል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንደሚሉት የገና ዛፎችን ልዩልዩ ቀለም ባላቸው መብራቶች አስጊጦ ማክበርን አውቀውትና ሃይማኖታዊ ሚስጥሩ ገብቷቸው እንዳልሆነም ይናገራሉ።

አብዛኞቹ ቤትን ስለሚያደምቅና ደስ ስለሚል ብቻ እንደሚያደርጉት ነው የሚናገሩት።

''አውቄው ሳይሆን ያው የገና ክሪስመስ ትሪ በጣም ደስ ስለሚል በቤቴ ወስጥ አደርጋለሁ። የእኛ ባህል አይደለም ብዬ ነው የማምነው፤ ያው ቤቱን ስለሚያስውብ ነው '' የምጠቀመው የምትለው ወይዘሮ ሰዓዳ በላይ ነች፡፡

ወይዘሪት አበባ ከበደ በበኩላቸው ከክሪስማስ ትሪ ይልቅ የተፈጥሪ ጽድ  ምርጯ ቢሆንም በመከልጀከሉ  መጠቀም እንዳልቻለች ስታስረዳ ሀይማኖታዊ ትርጉም ስከለመኖሮ  ምንም እንደማታውቅ ታስረተዳለች፡፤

 በቅርቡ እየተለመደ የመጣው የገና ዛፎችን ልዩልዩ ቀለም ባላቸው መብራቶች አስጊጦና ውድ ጌጣጌጦችን አድርጎ ማስዋብ ኃይማኖታዊ እንዳልሆነ አባቶች ይናገራሉ።

በኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጳጳስ ብጹዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ እንደሚሉት የገና በዓል ከዋዜማው ጀምሮ በማህሌት፣ በቅዳሴ፣ በዝማሬና በሌሎች ቤተክርስቲያናዊ ስርዓት ይከበራል።

ምዕመናንም  ከቤተክርስቲያን መልስ የታመሙትንና የታሰሩትን  በመጠየቅ፣ የተቸገሩትን በመርዳት፣ ጌታ በግርግም መወለዱን የሚያመክቱ ስርዓቶችን በማከናወን ፣ በጌታና በሎሌ መካካል ልዩነት እንደሌለ የሚያሳየውን የገናን ጨዋታ በመጫወትና ስጦታ በመሰጠጣት ያከብራሉ።  

እነዚህ ኃይማኖታዊ ሲሆኑ የገና ዛፍ ቤት ሊያደምቅ፣ ሲያዩትም ሊያምር ይችላል የሚሉት አባት፣ ነገር ግን የጌታን ልደት የሚያወሳ አንዳች ኃይማኖታዊ ትስስር እንደሌለው ይናገራሉ።

"የገናን ዛፍ ገዝተው ውድ በሆኑ ጌጦች አስውበው የሚያከብሩት ሌሎች አገሮች ናቸው፤ እነርሱ ያራሳቸው የሆነ ምሳሌ ሊኖራቸው ይችላል፤ እኛ ደግሞ የራሳችን ውብ ባህል ያለን በመሆኑ በሌሎች ተጽእኖ ስር መውደቅ የለብንም" ብለዋል።

"ቤተክርስቲያናችን ጌታችን በበረት እንደተወለደ፤ በግርግም እንደተኛ ጨርቅ ተጠቅልሎ ከከብቶች ትንፋሽ ሙቀትን እንዳገኘ፤ ቦታው በብርሃን ተሞልቶ መላዕክት ከሰዎች ጋር በአንድነት እንደዘመሩ፤ እንጂ የጽድ ዛፍ በአካባቢው እንደነበር የሆነ ታሪክ እንደተፈፀመ አያስተምርም" በማለትም ይገልጻሉ።

በተለይ በከፍተኛ ዋጋ ተገዝተው እቤት ውስጥ የሚሰቀሉ ዛፎችና ጌጣጌጦች "ያንን ገዝተው ማድረግ የማይችሉ ህጻናት ቀልብ ስለሚገዙ የደሃና የሃብታም ልዩነትንም ይፈጠራል፤ በታዳጊ ህጻናት ዘንድም ተጽእኖ ይፈጠራል" ብለዋል።

የጌታ ልደት ጌታና ሎሌ መላዕክትና ሰው በአንድነት የዘመሩበትና ፈጣሪን ያመሰገኑበት በመሆኑና በሰዎች ዘንድ ልዩነት እንደሌለ ያሳዩበት በመሆኑ ከዚያ ውጭ የሚከናወኑ ተግባራት ሃይማኖታዊ ይዘቱን ያስለቅቀዋል።

ቀስ በቀስ ገፍተው በሚገቡ ባዕድ ድርጊቶች ምዕመናን የራሳቸው ባህላዊ እሴት እንዳያጡና ከእምነታቸው እንዳይስቱ ከኃይማኖት አባቶች፣ ከመንግስትና ከባለድርሻ አካላት ሰፊ ስራ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም