ለውጡን ከዳር ለማድረስ ሁሉም የድርሻው ሊወጣ እንደሚገባ ተጠቆመ

69

ሰመራ  ታህሳስ 28/2011 በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ከዳር እንዲደርስ ሁሉም በየደረጃው የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

አክቲቪስት ዩሱፍ ያሲን  " የማንነት ፖለቲካ አንደምታዎችና የኢትዮጵያ እጣፈንታ" በሚል ርዕስ ዙሪያ ትናንት ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ  ማህበረሰብ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት አክቲቪስቱ እንዳሉት የባህልም ሆነ የእምነት ልዩነቶች ሀገራዊ የጋራ እሴቶችን በማያፈርስ መልኩ ተጣጥመው መሄድ በሰላም ተቻችሎ አብሮ ለመኖር ዋስትና ነው

ሆኖም ባለፉት 27 ዓመታት መንግስት በሀገሪቱ ሲከተል በነበረው ብሔርን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ልዩነቶች ላይ አብዝቶ በመስራቱ የጋራ የሆኑ ብሔራዊና ሀገራዊ እሴቶች መሸርሸራቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ዜጎች አብረው በሰላም መኖር በማይችሉበት ደረጃ ደርሰው ሀገሪቱ ወደ ብሔር ግጭት ለመግባት ጫፍ ደርሳ እንደነበር አመልክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር ወደስልጣን ከመጡ ወዲህ እየተወሰደ ባለው ተከታታይ የማሻሻያ እርምጃዎች የነበሩ አስፈሪ ግጭቶች እየረገቡ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን አክቲቪስት ዩሱፍ ተናግረዋል፡፡

በተለይም ባለፉት ዓመታት መንግስት ከፌዴራል ስርዓቱ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎችን ለመፍታት በቅርቡ ያቋቋመው ኮሚሽን እያጋጥሙ ላሉ ችግሮች እልባት ለመስጠት አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተጀመረው ሀገራዊ የለውጥ ሂደት ከዳር እንዲደርስ ሁሉም የራሱን ድርሻ በሚገባ ተረድቶ ተገቢውን ሚና ለመጫወት ሀሳቡን በግልጽ አውጥቶ መወያየት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ግልጽ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ትውልዱ ሐሳቡን በነጻነት የመግለጽ ባህል እንዲያዳብርና የጋራ ሀገራዊ አመለካከቶች እንዲጎለብቱ ተግተው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አመለክተዋል፡፡

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አደም ቦሬ በበኩላቸው በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ያሉበትን ክፍተቶች ለይቶ በመሙላት ጠንካራ ጎኑን ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለውጡ የህብረተሰቡን ጥያቄ በሚመልስ አግባብ ወደፊት እንዲራመድ በማድረግ በኩልም የሁሉም ዜጋ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ጠብቆ ለማቆየትና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቡ የጎለበተ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተማሪዎችና የአካባቢውን ህብረተሰብ ማወያየቱን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ከዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ መሰጡን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም