የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው የህብረተሰቡን የልማትና የለውጥ እንቅስቃሴ ሊያጠናክር ይገባል፡-አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

1125

ባህርዳር ታህሳስ 28/2011 የዘንድሮ የበጋ ወቅት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የህብረተሰቡ የልማትና የለውጥ እንቅስቃሴ የሚጠናከርበት ሊሆን እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ።

በምዕራብ አማራ የሚገኙ የዞንና የወረዳ አመራሮች የተሳተፉበት የ2011 የተፈጥሮ ሃብት ልማት የንቅናቄ መድረክም በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተሳተፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንደገለጹት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ የጋራ ጥቅም ያለው ሲሆን ውጤቱም በሂደት የሚታይ ነው።

አመራሩ ይህን ለህዝብ ማስገንዘብ እንዳለበት ገልጸው ባለፉት ዓመታት በክልሉ በህብረተሰቡ ሙሉ ተሳትፎ በተሰሩ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች የመሬት ለምነት እየተመለሰ መምጣቱን ተናግረዋል።

” በአሁኑ ወቅት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአንዳንድ አካባቢዎች በለሙ ተፋሰሶች ላይ ጉዳት የማድረስ ሁኔታ ስለሚስተዋል ህብረተሰቡ ሃብቱን እንዲጠብቅ አመራሩ ማስገንዘብ ይኖርበታል” ብለዋል።

በተያዘው የበጋ ወቅት የሚካሄደው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራም ህብረተሰቡ የልማትና የለውጥ እንቅስቃሴውን ከእዚህ ቀደሙ በተሻለ ሁኔታ የሚያጠናክርበት ሊሆን እንደሚገባም አቶ ገዱ አስገንዝበዋል።   

ህዝቡን ከድህነትና ኋላ ቀርነት በዘላቂነትለማላቀቅም አንድነቱን በማጠናከር ለለውጥና ለልማት እንዲነሳሳ የማዘጋጀት ሥራን አመራሩ የተለየ ትኩረት እንዲሰጠውም አሳስበዋል።

“ሁሉም አመራር የግብርና ባለሙያዎችን በማትጋት፣ የቀበሌ አመራሩን በማንቀሳቀስና በመምራት ኃላፊነቱን በቁርጠኝነት ሊወጣ ይገባል” ብለዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ማርቆስ ወንዴ በበኩላቸው ከ6 ሺህ 800 በሚበልጡ ተፋሰሶች ላይ ከጥር 2 ጀምሮ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ለመጀመር በቂ ዝግጅ መደረጉን ገልጸዋል።

“ከ471 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የሚከናወኑ የጋራና የማሳ ላይ ዕርከንና ሌሎች ሥራዎች በጥራትና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲከናወኑ የአመራሩ ድርሻ የጎላ ነው” ብለዋል።

አመራሩ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራው የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ እንዲከናወን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አቶ ማርቆስ እንዳሉት በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራው የሚሳተፍ የሰው ኃይልና የሥራ ቁሳቁስ የመለየት ሥራው ተጠናቋል።

“በአገሪቱ እየተስተዋለ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በህዝቡ ተሳትፎ ተሰርተው ለውጤት የበቁ ተፋሰሶች በአንዳንድ አካባቢዎች የቀበሌና የወረዳ አመራሮችን መቀየርን ተከትሎ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው” ብለዋል።

ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ፣ ማዕከላዊ፣ ምዕራብና ሰሜን ጎንደር ዞኖች ችግሩ ጎላ ብሎ ከሚታይባቸው መካከል እንደሚገኙበትም ጠቁመዋል።

በብዙ ልፋትና ድካም ተሰርተው ለውጤት የበቁ ተፋሰሶች እየደረሰባቸው ካለው ውድመት ለመታደግ አመራሩ ህዝቡን በማወያየት ፈጥኖ ሊታደጋቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊና የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን አበጀ የዘንድሮውን የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ለማከናወን በዞኑ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል በለሙ ተፋሰሶች በአንዳንድ ሰዎች እያደረሰ ያለውን ጥፋት ለመታደግ አመራሩ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት አድርጎ ማስቆም መቻሉን ተናግረዋል።    

የአዊ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው በበኩላቸው በአንዳንድ የዞኑ ወረዳዎች ማን ይነካናል በሚል የለማውን ተፋሰስ የማውደም ሥራ ተጀምሮ እንደነበረና በአሁኑ ወቅት ችግሩን በመነጋገር ማስቆም መቻሉን አመልክተዋል።

የዘንድሮ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራንም  ህብረተሰቡ ከአካባቢው ርቆ ሳይሄድ በየቀበሌው እንዲሰራ መታሰቡንም ነው የገለጹት።

የዘንድሮው ዓመት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በክልሉ በዋግህምራ ዞን ጋዝጊብላ ወረዳ ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት እንደሚጀመር ታውቋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በህብረተሰብ ተሳትፎ በ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ መከናወኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃን ጠቅሶ የዘገበው ኢዜአ ነው።