በማይጨው ከተማ የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥና የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዲፈቱላቸው ነዋሪዎች ጠየቁ

71

ማይጨው ታህሳስ 28/2011 በማይጨው ከተማ የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥና የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዲፈቱላቸው ነዋሪዎቹ ጠየቁ፡፡

የከተማው አስተዳደር ከ400 በላይ ከሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ከአገልግሎት አሰጣጥና ከመሰረተ ልማት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ትላንት ተወያይቷል፡፡

የከተማው ነዋሪ አቶ ገብረስላሴ ከበደ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት በከተማው የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነትን ለማስፋፋት የሚሰጠው አገልግሎት ደካማ ነው፡፡

ወጣቶች የሥራ ዕድል ካላገኙ በሂደት ለከተማዋ ፀጥታ መታወክ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡

ለወጣቶቹ የብድር አገልግሎት አሰጣጥ ያለው ረዥም ውጣ ውረድ ወጣቶች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ንጉስ ተስፋይ ናቸው፡፡

በማዘጋጃ ቤት የሚታየው የአሰራር ግድፈት ተገልጋዮችን ለምሬት እየዳረገ መሆኑ የገለጹት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አሸናፊ ዳርጎ ናቸው፡፡

በከተማው የሚኖሩ ከ370 የንግድ ማህበረሰብ አባላት ከ13 ሚሊዮን በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከል ለመገንባት ያቀረቡት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱን ገልጸዋል፡፡

በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ገብሩ ህንደያ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ዓመታዊ የንግድ ግብር ክፍያ የንግዱ ማህበረሰብ አቅም ያገናዘበ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

ሌላው የውይይቱ ተሳተፊ አቶ ህሉፍ ታደሰ እንዳሉት ከገጠር ወደ ከተማው የተካለሉ መንደሮች እስካሁን ድረስ የመጠጥ ውሃና የኤሌክትሪክ መብራት ባለማግኘታቸው እየተቸገሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በከተማው የሚሰሩ የድንጋይ ንጣፍ መንገዶችና ሌሎች የተፋሰስ ልማት ሥራዎችም የጥራት ችግር እንደሚስተዋልባቸው ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት፡፡

የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ጻዲቅ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ ከገጠር ወደ ከተማ ለተካለሉ መንደሮች የኤሌክትሪክና የመጠጥ ውሃ ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

የማዘጋጃ ቤቱን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እየተሰራ ቢሆንም አሁንም ችግሮች መኖራቸውን አምነዋል።

"በአሁኑ ጊዜ የማዘጋጃ ቤቶችን አደረጃጀት ለማዘመን አዲስ ሪፎርም እየተዘጋጀ ነው" ያሉት አቶ አሸናፊ፣ ረፎርሙ ተግባራዊ ሲደረግ የአሰራር ግድፈቶች ይወገዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡

የማይጨው ከተማ ከንቲባ አቶ አታክልቲ ፀጋይ በበኩላቸው በከተማው በመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ለሚታየው የጥራት ጉድለት በዋናነት የግንባታውን ሂደትን የሚከታተሉ መሀንዲስ ችግር መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎችን የሚከታተሉ መሀንዲሶች ስራቸውን በአግባቡ የሚወጡበት አዲስ አሰራር ተቀይሶ ወደስራ እተገባ በመሆኑ ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የመንግስት የግብር ገቢ በአግባቡ ካልተሰበሰበ አንዳችም የልማት ሥራ ማከናወን ስለማይቻል ደረሰኝ በማይቆርጡ ነጋዴዎች ላይ የሚጣለው ቅጣት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

በከተማው በማህበር ተደራጅተው የሕንፃ መስሪያ ቦታ ጥያቄ ያቀረቡት የንግድ ማህበረሰብ አባላት ባቀረቡት ፕሮጀክት ግድፈት ምክንያት እስካሁን ምላሽ እንዳላገኙና ችግሩ የአስተዳደሩ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

የማህበሩ አባላት ፕሮጀክቱ እንዲሻሻል የተነገራቸውን የማስተካከያ  ሐሳብ  አሟልተው ከቀረቡ  በከተማ አስተዳደሩ በኩል የመስሪያ ቦታውን እንደሚፈቀድላቸው አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም