መንግስት የጀመረውን ሀገራዊ አንድነትና ሰላም የማስፈን በጎ ተግባር ማጠናከር ይገባል-የኃይማኖት አባቶች

98

አዲስ አበባ ታህሳስ 28/2011 መንግስት የጀመረውን ሀገራዊ አንድነትና ሰላም የማስፈን በጎ ተግባር ማጠናከር እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

የኃይማኖት አባቶች የዘንድሮን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ በመልዕክታቸው ቤተ ክርስቲያን በህዝቦች አንድነት፤ ሰላም፤ በዜጎች እኩልነትና ሰብአዊ መብት መከበር የጸና አቋም አላት ብለዋል።

ይሁንና አሁን ያለው የፖለቲካ ሃይሎች ሽኩቻና አንዱ አንዱን ጥሎ ለማለፍ የሚያደርገው ቅድምድሞሽ ችግር እያስከተለ እንደሆነም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ካጋጠማት የሰላም መደፍረስ በአፋጣኝ እንድትወጣ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ሰፊ የውይይት መድረክ በመክፈት በሀገር አንድነት፤ በዜጎች እኩልነትና ሰብዓዊ መብት መከበር የጋራ አቋም በመያዝ ሰላምን ሊያረጋግጡ ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ወገን ወገኑን ከማፈናቀል፤ ከማሳደድና መንገድ ከመዝጋት ሊቆጠብ ይገባል ብለዋል አቡነ ማቲያስ።

በተለይ ወጣቱ ትውልድ ‘ግሎባላይዜሽን’ ካመጣው የባህል ወረርሽኝ፤ ከሱስና ከአደንዛዥ እጽ ተቆጥቦ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም በትጋት መስራ እንዳለበት መክረዋል።

 “ሰላም በምድር ሁሉ ይሁን” የሚል የቤተ ክርስቲያን መርህ ነው ያሉት ፓትሪያርኩ፤ በዓሉን ስናከብርም በመተሳሰብና በመረዳዳት እንዲሆን በአደራ ጭምር አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ በበኩላቸው ህብረተሰቡ የአገርን ሰላም በማስጠበቅ ልማትን እንዲያሳድግ በቤተ ክርስቲያኗ ስም ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ ወጣቶች እምቅ ኃይል ያላቸውና ነገሮችን የመፍጠርም ሆነ የመለወጥ ብቃት ያላቸው መሆኑን የገለጹት ካርዲናሉ፤ ለሰላም መጠበቅ የነገሮችን ሁኔታና አመጣጥ አይተው  በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ ጥበቡን እንዲጠቀሙት ልንረዳቸው ይገባልም ብለዋል።

መንግስት በአሁኑ ጊዜ እያደረገ ያለውን የሰላም ተግባር ሁሉም በትጋት የህግ የበላይነትነት በማስከበር  ማስቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ካርዲናሉ አክለውም የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ስናከብር ድሆችንና አቅመ ደካሞችን፤ ህሙማንና ረዳት የሌላቸውን በማስታወስ በጋራ መሆን እንዳለበትም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮችም እንኳን ለ2011 ለጌታችንና ለመድሃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈው በዓሉም የሰላምና የደስታ እንዲሆን ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም