አብሮነትን በሚያጎልብት መንገድ የገናን በዓል እናከብራለን ፡-የመቱ ከተማ ነዋሪዎች

56

መቱ ታህሳስ 28/2011 በአካባቢያቸው የገና በዓልን ወጪን በመቆጠብ  አብሮነትን በሚያጎለብት ዝግጅት እንደሚያከብሩት በመቱ ከተማ ነዋሪዎች  ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት በዓሉን  ወዳጅ ዘመድና ጎረቤት የሚቀራረቡበትና በጋራ የሚያከብሩት በመሆኑ በአብሮነት ስሜት ለማክበር ተዘጋጅተዋል።

አቶ ለማ መንግስቴ በኢሉአባቡር ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት የሚሰሩ የመቱ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ  ገናና ሌሎችም ክብረ በዓላት  የተለያዩ ባህል፣ ኃይማኖትና ቋንቋ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በማገናኘት ረገድ   አስተዋጽኦ  እንዳለው በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።

በተለይም  የገና በዓልን ከተያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር አብረው በመሆንና እየጨመረ የመጣውን   የገበያ ዋጋ ለመቋቋም  ገቢን ባገናዘበ መልኩ ወጪን ቆጥበው  እንደሚያከብሩት ተናግረዋል።

በከተማው በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ዘሪሁን ወዳጆ በበኩላቸው የገና በዓል ከተለያዩ አካባቢዎች ወዳጅ ዘመድን የሚያገናኝ በዓል በመሆኑ በጉጉት እንደሚጠብቁት ተናግረዋል።

አስተያያት ሰጪው እንደገለጹት በዓሉን  በደመቀ ሁኔታ ከጎረቤቶቻቸውና ከዘመዶቻቸው ጋር ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅት አድርገዋል፡፡

" የአረፋን በዓል ከሙስሊም ወንድሞቻችን ጋር አብረን እንዳከበርነው ሁሉ ገናን  በዓልም በጋራ እናከብራለን"ብለዋል።

በከተማው በበዓሉ ዋዜማ  በዋለው  ገበያ አቅርቦቱ በብዛት እንዳለና ከዋጋም ጋር ተያይዞ  በዶሮ ዋጋ ላይ መጠነኛ ቅናሽ መታየቱን በዶሮ ንግድ የተሰማሩ አቶ ታዬ ይታፋ ተናግረዋል።

ትልቅ አውራ ዶሮ ከዚህ ቀደም  አራት መቶ ብር ይሸጥ የነበረው አሁን   ወደ 300 ብር ዝቅ ብሎ እየተሸጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

ወጪን ቆጥበው  የአብሮነት እሴታቸውን በሚያጎለብት ባህላዊ ሰነስርዓት  በዓሉን  እንደአቅማቸው ለማክበር መዘጋጀታቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም