የፊንጫ አስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

64

ነቀምቴ ታህሳስ 28/2011 የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች በግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብና የአልባሳት ድጋፍ አደረጉ ፡፡

ሠራተኞቹ ትናንት ድጋፍ ያደረጉት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ወገኖች ነው፡፡

ፋብሪካውንና የፋብሪካውን ማህበረሰብ ወክለው ድጋፍ ያደረጉት አቶ ከበደ ነጋሣ እርዳታውን ለምስራቅ ወለጋ ዞን የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት አስረክበዋል።

በእዚህ ወቅት እንደተናገሩት ተፈናቃዮቹ የጥፋት ኃይሎች ባቀነባበሩት ሴራ በርካታ ዜጎች ያለጥፋታቸው ከሞቀ ቤታቸውና ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ።

ተፈናቃዮች ስላሉበት ሁኔታ የፋብሪካው ሠራተኞች በመወያየት ከደመወዛቸው ቀንሰው 865 ሺህ 351 ብር የሚገመት 385 ኩንታል የስንዴ ዱቄት፣ 50 ኩንታል ስኳር፣ 550 ሊትር የምግብ ዘይት እና ከፋብሪካው ሠራተኞች የተሰበሰቡ 4 ኩንታል የተለያዩ አልባሳትን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ዕርዳታው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክትዋል።

የምስራቅ ወለጋ ዞን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳርጌ ጉደታ እርዳታውን ሲረከቡ እንደተናገሩት “የፊንጫ ስኳር ፋብሪካና ሠራተኞች ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን በተግባር አሳይቷል” ብለዋል።

ረጅም መንገድ አቋርጠው በነቀምቴ ተገኝተው ላደረጉት ዕርዳታም በራሳቸውና በምስራቅ ወለጋ ዞን ሕዝብ ስም አመስግነዋል፡፡

የነቀምቴ አባገዳዎችም የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉት ወገኖች ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው መርቀዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም