ለበግና ፍየል ዋጋ መናር የደላሎች ሚና ከፍተኛ ነው – ነጋዴዎች ና አርሶ አደሮች

652

ታህሳስ 27/2011 በበግና ፍየል ገበያ ላይ የተሰማሩ ደላሎች ለዋጋ መናር መንስኤ መሆናቸውን ያናገርናቸው ነጋዴዎችና አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

በብርጭቆ የበግና ፍየል ገበያ ማዕከል እና በዊንጌት በግ ገበያ ስፍራ ያገኘናቸው  ነጋዴዎችና አርሶ-አደሮች እንደሚሉ ከሆነ የበግና የፍየል ዋጋ በየጊዜው ጭማሪ እያሳየ የመጣው በህገ-ወጥ ደላሎች መሆኑን ነው፡፡

በብርጭቆ በግ ገበያ  ማእከል ያገኘናቸውና ከአርሲ ሶጉሬ መምጣታቸውን የሚናገሩት አርሶ አደር አደም ኢስማኤል በአሁኑ ወቅት የአንድ በግ ዋጋ እስከ አምስት ሺህ ብር መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

ከገጠር የሚመጡ በጎች የተለያዩ ወጪዎች ያሉባቸው ቢሆንም ደላሎች በመሀል እየገቡ ዋጋውን እያናሩት በመሆኑ አርሶ አደሩ የልፋቱን ያህል እያገኘ አይደለም ያሉት አርሶአደር አደም በጎቻቸው እንደሚሰረቁና ለማሳደሪያ በረት በቀን ለአንድ በግ መቶ ብር እንደሚከፍሉ ተናግረዋል፡፡

ከጅማ አጋሮ እንደመጣ የሚናገረው ሌላው የበግ ነጋዴ ወጣት ቶፊቅ አባጅሀድ በግ ጭኖ ካመጣ በኋላ አንዳንድ ህገወጥ ደላሎች በጎቹን በፈለገው ዋጋ እንዳይሸጥ  እያደረጉ  መሆኑን  ይገልጻል፡፡

ደላሎቹ አንዳንድ ግዜ ሸማችን አፈላልገው እንደሚያገናኟቸው የተናገረው ወጣት ቶፊቅ በከተማው ውስጥ በቂ የማደሪያ ቦታ እና በቂ መኖ ባለመኖሩ በጎቹን ከበዓል ሰሞን በስተቀር በጊዜ ወደ ከተማ ይዘው እንደማይመጡም ነው የተናገረው፡፡

ከሀረር ፍየል እያመጣ እንደሚነግድ የነገረን አቶ ፈትሂ ሀጂ ፍየል ከሺህ ስምንት መቶ እስከ ስምንት ሺህ ብር እየተሸጠ  እንደሚገኝና ለዋጋው መናር በየአካባቢው ያሉ ደላሎች ምክንያት መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

“እኛ ነጋዴዎቹ ከአርሶ አደሩ መግዛት የማንችልበት ሁኔታ ተፈጥራል” የሚሉት አቶ ፈትሂ ደላሎች ከአርሶና አርብቶ አደረ በትንሽ ዋጋ እየገዙ በከፍተኛ ዋጋ ስለሚሸጡ ዋጋው እየናረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡  

ከአርሲ አካባቢ በጎችን ጭኖ እንደመጣ የተናገረው ከድር ጠሀ የበጎች ማደሪያ ስፍራ አለመኖር  ምክንያት በግ በሚያድርበት ወቅት አንድ መቶ ብር እንደሚከፍልና የበአል ሰሞን ክፍያው በቀን ሁለት መቶ ብር እንደሚሆን ተናግሯል፡፡

በቂ መኖ አለመኖርና መኖ ቢኖርም እንኳን የዋጋው ከፍተኛ መሆን በበግ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንዲኖረ አድርጎታልም ብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የግብይት ክትትል ተሳታፊዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን በቀለ ስለሁኔታው ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ከተማ አስተዳደሩ የተነሱትን ችግሮች ለማቃለል የተለያዩ ተግባራትን አያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በህገወጥ ደላሎች አማካኝነት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማስወገድ የገበያ ትስስር እንዲኖር ከሸማቾች ማህበራትጋር የማስተሳሰር ስራ እያከናወነ  እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ የበግና ፍየል ማአከላትን እየገነባ እንደሚገኝ የተናገሩት ዳይሬክተሩ ስራ ከጀመረው የቃሊቲ በግና ፍየል ገበያ ማዕከል በተጨማሪ  በየካ፣ አቃቂና ቦሌ ክፍለ ከተሞች ላይ የገበያ ማዕከላትን ከአምስት ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ እየተገነባ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ብርጭቆ የበግና ፍየል ገበያ ማዕከል በዘመናዊ መንገድ ደረጃውን የማሳደግ ስራም እየተከናወነ መሆኑን ነው አቶ ሰለሞን የጠቆሙት፡፡

በማዕከላቱ ውስጥ የማደሪያ በረት እየተገነባ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት የተደራጁ ወጣቶች ለማዕከላቱ መኖ እንዲያቀርቡ  እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡