የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን በመቀሌ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት

121

መቀሌ ታህሳስ 27/2011የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን አባላት መቀሌ አሉላ አባነጋ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በመቀሌ 70 እንደርታና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ስፖርት ክለብ ደጋፊዎችና የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች አቀባበል ተደረገላቸው፡፡

የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን አባላትም በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ክልል እግር ኳስ  ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አባዲ አባይ በአቀባበሉ ስነ ስርዓት ተገኝተው  ለፋሲል ከነማ ቡድን አባላት እቅፍ አበባ አብርክተውላቸዋል፡፡

የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን መሪ ሐብታሙ ዘዋለ እንደገለጸው "የመቀሌ ከተማ ህዝብ  በተለይ የወጣቶች አቀባበል ፍቅርና አንድነት ምን እንደሆነ አሳይተውናል" ብለዋል።

ተቋርጦ የቆየው ውድድር አሁን በመጀመሩ ደስተኛ መሆኑን የተናገረው  ቡድን መሪው "እኛም በተራችን  ስፖርተኛን በፍቅር ለመቀበል ዝግጁ ነን" ብሏል፡፡

ጨዋነት የተሞላበት ስፖርታዊ ውድድር ለማካሄድ የስፖርት ደጋፊዎች ማህበር በትኩረት  ሊሰሩ እንደሚገባ ቡድን መሪው አመልክቷል፡፡

የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ እግር ኳስ ክለብ ስራ አስፈፃሚ መርሃዊ ሃይለስላሴ በበኩሉ "የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን አባላት ወደ መቀሌ መምጣታቸው እኔ ብቻ ሳይሆን ህዝቡም የተሰማው ደስታ ልዩ ነው" ብለዋል፡፡

ወልዋሎ አድግራት ዩኒቨርስቲና ፋሲል ከነማ ነገ በሚያደርጉት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ  ደጋፊው ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ እንዲደግፉ ስራ አስፈጻሚው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም