ኢትዮጵያና ሱዳን ለቀጣናዊ ምጣኔ ኃብታዊ ውህደት በጋራ እንደሚሰሩ መሪዎች ተናገሩ

69
ሚያዚያ 25/2010 ኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነታቸውን  በማጠናከር ለቀጣናዊ  ምጣኔ ኃብታዊ ውህደት በጋራ እንደሚሰሩ የአገሪቱ መሪዎች ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ ትላንት ማምሻውን ከሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ጋር በሱዳን ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ተወያይተዋል። ከውይይታቸው በኋላ፤ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀውን የሁለቱን አገሮች ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ሁለቱ መሪዎች አረጋግጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያና ሱዳን ባላቸው የሕዝብ ብዛትና የጂኦ ፖለቲካ አቀማመጥ የተነሳ ለቀጣናው ሁለንተናዊ እድገትና ለውጥ ወሳኝ ናቸው። አገሮቹ ባለፉት ዓመታት በተለይም በምጣኔ ኃብት ትብብር መስኮች ላይ የላቀ አዎንታዊ ለውጥ ማስመዝገባቸውን ገልጸው 'ይህም ሊቀጥል ይገባዋል' ብለዋል። በጋራ የድንበር መርኃ ግብር፣ በኃይልና በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰሩትን ሥራዎች ለአብነት ጠቅሰው፤ 'አሁንም በቀጣይ በርካታ ሥራዎችን መሥራት ይኖርብናል' ነው ያሉት። ለዚህም ደግሞ በሁለቱም አገሮች መካከል ያለው የህዝብ ፍላጎት ለመተባበርና ያሉትን ችግሮች በጋራ ለመፍታት ግፊት የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል። ስትራቴጂክ አጋርነቱን በማስቀጠል ለቀጣናውም ሆነ ለአፍሪካ ሰላምና ብልጽግና በጋራ ለመሥራት መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑንም ዶክተር አብይ ጠቁመዋል ። 'ባለፉት ዓመታት በርካታ ድሎች ቢመዘገቡም ከዚህ በኋላ በርካታ ሥራዎች መሠራት አለባቸው'  በማለት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰላምና በደህንነት እንዲሁም በብልጽግና የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት ስትራቴጂካዊ  ግንኙነቱን ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል። ሁለቱ አገሮች ግንኙነታቸውን በማጠናከር ለቀጠናውና ለአፍሪካ ሰላምና ብልጽግና ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል። 'የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር መሥራት አለብን' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሮቹ ወዳጅነት በህዝቦች አዕምሮና ልብ ጭምር የተቀረጸ መሆኑን አንስተዋል። አገሮቹ ድንበር ከመጋራት ባለፈ ቋንቋንና ሌሎች  የጋራ እሴት ያላቸው በመሆኑ ይበልጥ ለመቀራረብ የሚያስችል ዕድል መኖሩን አስረድተዋል። የሁለቱ ሕዝቦች በአባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን መስተጋብር ያህል በመንግሥታትም ደረጃ መኖሩን ጠቁመው የወንድማማችነት መንፈሱ በተለይም የሦስትዮሽ ውይይቱ እንዲጎለብት ጠይቀዋል። ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ለያዘችው አቋም አመስግነው፤ ይህም ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። እስካሁንም አገሮቹ ከምጣኔ ኃብት ትብብር በተጨማሪ በቀጠናዊ ሰላምና ደህንነት ጉዳይ ላይ ምሳሌ የሚሆን ሥራ መሥራታቸውን ጠቁመው አንድነቱ ተጠናክሮ ከቀጠለ የማይሳካ ነገር እንደማይኖር እምነታቸውን ገልጸዋል። የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር በተመሳሳይ የአገሮቹን ታሪካዊ ግንኙነት አሁን ካለበት ደረጃ ወደ ላቀ ምዕራፍ ማሸጋገር ቀጣይ አጀንዳ መሆኑን ተስማምተዋል። አገሮቹ በምጣኔ ኃብት ትስስር ረገድ አበረታች ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው 'ለዚህም ደግሞ የአገሮቹ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሚናው የጎላ ነው' ብለዋል። በቀጣይም አሁን ላይ ያለውን ትብብር በእጥፍ ለማሳደግና የትብብር መስኩንም ለማስፋት እንደሚሰሩ ነው ያረጋገጡት። 'በቀጣይም በመሪዎች ደረጃ ውይይት በማድረግ በአገሮቹ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ እንሰራለን' ብለዋል። በባቡር መስመር ዝርጋታና በኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ዘርፍ በጋራ የሚከናወነው ተግባር ለቀጣናዊ ውህድት ሚናው ከፍተኛ እንደሚሆን ነው ፕሬዚዳንቱ የገለጹት። በታላቁ የህዳሴ ግድብ መርህ ላይ ጽኑ እምነት እንዳላቸውና ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር የምታካሂደው የሦስትዮሽ ውይይትንም  አገራቸው ጠቀሜታውን ትቀበላለች ነው ያሉት። 'ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ ኃላፊነት ይጥልብናል' ያሉት ፕሬዚዳንቱ በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት በጋራ እንሰራለን ብለዋል። ለዚህም በጋራ አልያም ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንገግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) በኩል እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ በመጠቆም። በሌላ በኩል ኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ አቋም ያላቸው አገሮች እንደሆኑና በተለይም በአፍሪካ የምዕራባውያኑን ተጽዕኖ ለማሳነስ ያላቸውን እንቅስቃሴ ለአብነት ጠቅሰዋል። ለሥራ ጉብኝት ካርቱም የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዛሬው ዕለት ከግብርና ጋር በተያያዘ የመስክ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም