ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛ ትሰራለች -ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ

78
ሀዋሳ ግንቦት 18/2010 ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛ ትሰራለች ሲሉ የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከሩዋንዳ ጋር በመሆን የተሻለች አፍሪካን ለመገንባት እንደምትሰራ ገልጸዋል። ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በኢትዮጵያ በነበራቸው የሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል። በኢንዱስትሪ ፓርኩ በነበራቸው ቆይታም በዋናነት በጨርቃ ጨርቅና የህጻናት ንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን አምርተው ወደ ውጭ በመላክ ላይ የተሰማሩ ዓለም አቀፋዊ ኩባንያዎችን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል። ፕሬዝዳንቱ ከጉብኝቱ በኋላ በሀዋሳ ከተማ በተደረገላቸው የእራት ግብዣ በሃድያ ባህላዊ ልብስ በተሰራ ሱፍ ደምቀው የቀረቡ ሲሆን፤ አንድ ከብት ከነ ጥጃዋ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል። ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜም የሩዋንዳ ባህላዊ ጭፈራ እና ከነሙሉ ባህላዊ እሴቱ የሚያሳይ የስዕል ስጦታ ለጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ አበርክተውላቸዋል። ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በዚህ ወቅት እንዳሉት "የኢትዮጵያና የሩዋንዳ ህዝቦች ልብ ለልብ የተሳሰረ ወዳጅነት አላቸው"። በቀጣይም አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ይበልጥ እጅ ለእጅ ተያይዛ እንደምትሰራ ጠቁመዋል። በቅርቡም ሰፋ ላለ ጉብኝት ተመልሰው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ተናግረዋል። የተሰጠቻው ስጦታም በኢትዮጵያና ሩዋንዳ ህዝቦች መካከል የባህልና የትውፊት መመሳሰል መኖሩን እንደሚያሳይ ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከሩዋንዳ ጋር በመሆን አፍሪካን ለመቀየር እንደምትሰራ ገልጸዋል። ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በሩዋንዳ ብቻ ሳይሆን ሰላማዊና በኢኮኖሚ የተሳሰረች አፍሪካን ለመፍጠር እየሰሩ ያሉ መሪ መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ተናግረዋል። ሩዋንዳ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን  ማጽደቋ ለአፍሪካ ትስስር ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ለአብነት ያነሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ኢትዮጵያም ሩዋንዳን ተከትላ ስምምነቱን ለማጽደቅ ዝግጁ መሆኗን አውስተዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ስምምነቱን ያላጸደቁ አገራትም ሩዋንዳን ተከትለው በቅርቡ እንደሚያጸድቁ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በዓመት 250 ሚሊዮን የህጻናት ንጽህና መጠበቂያ የሚያመርተው ኦንቴክስ፤ የሸሚዝ ምርትን ሙሉ ለሙሉ ወደ ውጭ የሚልከው ታል አፓሬል ኩባንያ እንዲሁም ብትን ጨርቅ በፓርኩ ውስጥ ላሉ ኩባንያዎች የሚያከፋፍልና ወደ ውጭ የሚልከው ጄፒ ቴክስታይል በፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ከተጎበኙ ኩባንያዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም