ወጣቶች በሃገሪቱ ለተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ስኬታማነት ሊሰሩ ይገባል - የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ

89

ወልድያ ታህሳስ 27/2011 የአማራ ክልል ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት ነቅተው በመጠበቅ በሃገሪቱ ለተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ስኬታማነት ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ የሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አስገነዘቡ።

የቢሮው ኃላፊ ብርጋዴል ጀነራል አሳምነው ጽጌ ትናንት ከወልድያ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት እንደገለፁት በአገሪቱ ለተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ስኬታማነት የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት አማራው በክልሉ ውስጥም ሆነ በሌሎች ክልሎች ማንነቱን መሰረት ያደረጉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፀሙበት መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡

አሁን ላይ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደህንነት ሊያረጋግጥ የሚችል የለውጥ ብርሃን እየታየ ቢሆንም ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት ለውጡን ወደ ኋላ ለመመለስ እየተንቀሳሱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በየአካባቢው አለመረጋጋት በመፍጠርም የሰዎች ህይወት እንዲያልፍ፣ የአካል ጉዳት እንዲደርስ፣ ዜጎች ለፍተው ያፈሩት ሃብት እንዲወድምና ሰብአዊ ቀውስ እንዲከሰት እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

መንግስት ችግሩን በሰከነና ዘላቂነት ባለው መንገድ ለመፍታት ብርቱ ጥረት እያደረገ እንደሆነ አስታውቀዋል።

''የመንግስት ጥረት ሊሳካና ዳር ሊደርስ የሚችለው የወጣቱ የነቃ ተሳትፎ ሲታከልበት ነው'' ያሉት ሃላፊው ወጣቱ በተደራጀ መንገድ የጀመረውን አካባቢውን የመጠበቅና ሰላሙን የማረጋገጥ ስራ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የወልድያ ከተማ ነዋሪና የውይይቱ ተሳታፊ  አቶ ሰማው አከለ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል ህዝብን ክፉኛ ሲያማርሩና ግፍ ሲፈፅሙ የነበሩ አመራሮች አሁንም የለውጡ አካል ለመምሰል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

''እነዚህ አመራሮች  ተለይተው የማስተካከያ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል'' ያሉት አስተያየት ሰጪው ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በከፍተኛ አመራሮች የተጀመረው የማስተካከያ እርምጃ እስከታችኛው እርከን ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ወጣት ቴዎድሮስ አያሌው በበኩሉ ''በሕዝብ ላይ ግፍ የሰሩ አመራሮች አሁንም በስልጣን ላይ ስላሉ አጥፊና አልሚውን በአግባቡ ለይቶ ለውጡ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል'' ብሏል፡፡

ለውጡ ክቡር የሰው ህይዎት መስዋትነት የተከፈለበትና ህዝብ ታግሎ ያመጣው በመሆኑ አሁንም በህዝብ ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አስተያየት ሰጭዎቹ አስታውቀዋል።

ትናንት በተካሄደው ውይይት የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በብርጋዲዬል ጀኔራል አሳምነው ጽጌ የሚመራ ቡድን በቆቦና በመርሳ ከተሞችም ተመሳሳይ ውይይቶችን ማድረጉ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም