ሀገር አቀፉ የትምህርት ስልጠና ፍኖተ ካርታ ለተግባር ስልጠና ትኩረት ሊሰጥ ይገባል

51

ጎንደር  ታህሳስ 26/2011 ሀገር አቀፉ የትምህርት ስልጠና ፍኖተ ካርታ ለከፍተኛ ትምህርት የተግባር ስልጠና ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ በጎንደር ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አሳሰቡ፡፡

በፍኖተ ካርታው ላይ ግብአት ለማሰባሰብ የተዘጋጀ ውይይት በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አይቸው ታረቀኝ እንደተናገሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስራ ፈጣሪ ትውልድ ቀርጾ በማወጣት ረገድ ባለፉት ዓመታት ተጨባጭ ክፍተት ታይቶባቸዋል፡፡

ተማሪዎች ከንድፈ ሃሳብ በዘለለ በቂ የተግባር ክህሎት ጨብጠው እንዲወጡ በማድረግ ረገድ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተግባር ልምምድ የሚያካሂዱባቸው በቂ ማዕከላትና ተቋማት እንዲቋቋሙ በፍኖተ ካርታው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

በርካታ ተመራቂዎች የብቃት መመዘኛ ፈተናዎችን ለማለፍ የሚቸገሩት አሰልጣኞችም ፈታኞችም እራሳቸው ተቋማቱ በመሆናቸው ስለሆነ ይህ አሰራር በፍኖተ ካርታው ሊፈተሸ እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ መከተ ታምሩ ናቸው፡፡

" የብቃት መመዘኛ ፈተና በመስጠት በኩል የተለያዩ የሙያ ማህበራት ሊሆኑ ይገባል"  ያሉት አቶ መከተ ለሙያው ቅርበት ያላቸውና ቀጣሪዎቹም እነሱ በመሆናቸው ፍኖተ ካርታው ለሙያ ማህበራቱ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡

ወይዘሮ ህብስት ጥሩነህ የተባሉ የውይይቱ ተሳታፊ በበኩላቸው ከአንድ እስከ አራተኛ የክፍል ደረጃዎች በአንድ መምህር ብቻ ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች ተማሪዎች እንዲማሩ የሚያስገድደው አሃዳዊ የማስተማር ዘዴ በአዲሱ ፍኖተ ካርታ ሊቀር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዋ ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ ሲተገበር የቆየው አሃዳዊ የማስተማር ዘዴ ተማሪዎች ከተለያዩ መምህራን ማግኘት የሚገባቸውን እውቀትና ክህሎት የገደበና በመምህሩም ተቀባይነት ያልተሰጠው ነው፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ታደሰ ሙጨ እንዳሉት  አዲሱን ትውልድ ቀርጾ በማውጣት ረገድ ሰፊ ድርሻ ያለው የታሪክ ትምህርት ላለፉት ዓመታት በከፍተኛ ትምህርት እንዳይሰጥ ተከልክሎ መቆየቱ አግባብ ባለመሆኑ በፍኖ ካርታው ሊካተት ይገባል፡፡

የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር ትምህርትም ቢሆን ጠቃሚነቱ የጎላ ቢሆንም አተገባበር ላይ የነበሩት ጉድለቶች ተፈትሾና ስርዓተ ትምህርቱና የማስተማሪያ መጻህፍቱም ተገምግሞ ተጠናክሮ ሊሰጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን እርካቤ በበኩላቸው "  ላለፉት 25 ዓመታት ስራ ላይ የቆየው የትምህርት ፖሊስ ዳግም ተፈትሾ አዲስ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱ የትምህርት ስርዓቱን ጉድለቶች ለማረም ያስችላል" ብለዋል፡፡

መንግስት ፍኖተ ካርታው በህዝብ ውይይት ዳብሮ ስራ ላይ የሚውልበትን እያመቻቸ በመሆኑ የውይይቱ ተሳታፊዎች የሰጡት ግብአት የሀገሪቱን የትምህርት ስርዓት ለመቀየር ብሎም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ፣ሰራተኞች ፣ወላጆችና መምህራን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም