የደብረ ብርሃን አንኮበር የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ ተጀመረ

117

ደብረ ብርሃን ታህሳስ 26/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚካሄደው የደብረ ብርሃን አንኮበር የ42 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ ዛሬ ተጀመረ።

የመንገዱ ግንባታ የተጀመረው የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስና ሌሎች የመንግስት ስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ነው፡፡

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር መሃመድ አብዱርሃማን እንደገለፁት መንገዱ ከዚህ ቀደም ከ 6 እስከ 7 ሜትር ስፋት ባልበለጠ የጠጠር መንገድ ደረጃ ሲያገለግል ቆይቷል።

አሁን በአካባቢው እያደገ የመጣውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ወደ አስፓልት ኮንክሪት ለማሳደግ  ግንባታው ተጀምራል።

ግንባታው ሰንሻይን ኮንስትራክሽን የተባለ ሀገር በቀል የመንገድ ተቋራጭ ድርጅት የሚከናወን ሲሆን ኮር ኮንሰልቲንግ ኢንጅነርስ ደግሞ የማማከር ስራውን ያከናውናል።

የዚህ መንገድ ስፋት በከተሞች 17 ሜትር  በገጠር ደግሞ 10 ሜትር መሆኑን ኢንጅነር መሃመድ ጠቁመዋል።

አንጂነሩ እንዳሉት ግንባታው በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ  ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ይጠበቃል፤ ሙሉ ወጪውም በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው የመንገዱ ግንባታ በአጼ ሚኒሊክ መናገሻ በሆነችው አንኮበር መገንባቱ ለውጭና ለሃገር ውስጥ ቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የአካባቢውን የሰብል ምርት  ለመሃል አገር ገበያ በፍጥነት ለማቅረብ እንደሚግዝም አመልክተው "ከአጎራባች ክልል አፋር ጋራ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር ይረዳል "ብለዋል።

ግንባታው ተፋጥኖ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲውል የአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፍ እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ በሚኒስትር ማዕረግ  የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም ናቸው፡፡

በአካባቢው ያለው የአጼ ሚኒሊክ ሎጅ ባለቤት ኢንጅነር ተረፈ ራስወርቅ በበኩላቸው አካባቢው ታሪካዊ ቢሆንም ያለውን ሃብት ለመጠቀም በመንገዱ ምቹ ያለመሆን  ህብረተሰቡ ሲቸገር መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

መንገዱ እንዲሰራ ተደጋጋሚ ጥያቄ ይቀርብ እንደነበር አስታውሰው አሁን መንግስት ምላሽ መስጠቱን  አመስግነዋል፡፡

መንገዱ በተያዘለት ጊዜና ጥራት እንዲከናወን የአካባቢውን ማህበረሰብ በማስተባበር የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

በመንገድ ማስጀመሩ ፕሮግራም የተለያዩ የመንግስት ሃላፊዎችና የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝቷል።

ትናንትም በዞኑ  ከጣርማ በር መለያ፣ ሰፌድ ሜዳና ሞላሌ ወገሬ የ118 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ መጀመሩን ኢዜአ  ዘግቧል፡፡

ለዚሁ መንገድ ግንባታ ማስፈጸሚያ  አንድ ቢሊዮን 900 ሚሊዮን ብር መመደቡም ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም