በምእራብ ሸዋ ዞን ባለፉት አምስት ወራት ለ11 ሺህ 900 ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩ ተገለፀ

62

አምቦ ታህሳስ 26/2011 በምእራብ ሸዋ ዞን ባለፉት አምስት ወራት 11 ሺህ 900 ወጣቶች ወደ ስራ መግባታቸውን የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና የከተሞች ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ገለፀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ታደሰ ፌደሳ እንደገለፁት ወጣቶቹ ወደ ስራ የገቡት በ1ሺህ 532 ማህበራት በመደራጀት ነው ።

የሥራ ዕድል ከተፈጠርላቸው ወጣቶች መካከል 4 ሺህ 172  ሴቶች መሆናቸውን አቶ ታፈሰ ተናግረዋል ።

ወጣቶቹ ከተሰማሩባቸው የስራ መሰኮች መካከል ንግድ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ግንባታ፣ የከተማና የገጠር ግብርና፣ አገልግሎት፣ የማዕድን ልማት፣ የእንስሳት ማድለብና እርባታ ሥራዎች ዋነኞቹ ናቸው ።

ወጣቶቹ ስራ የሚጀምሩበት 18  ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የብድር ገንዘብ ፣ 492 ነጥብ 5 ሄክታር መሬትና 95 የማምረቻና የመሸጫ ሼዶች ተሰጥቶአቸዋል፡፡

የ143 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸውም ኃላፊው ተናግረዋል ።

የደንዲ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ቢሊሱማ ነጋሳ በሰጠው አስተያየት  "በዲግሪ ከተመረኩ ሁለት ዓመት ቢሆነኝም እስከ አሁን ስራ ማግኘት ባለመቻሌ ተቸግሬ ቆይቻለሁ " ብሏል።

አሁን ግን መንግስት ባመቻቸው እድል በመጠቀም  ከጓደኞቹ ጋር በግብርና ልማት  በመደራጀት አስፈላጊውን ስልጠና ወስዶ ወደ ስራ በመግባት እራሱንና ቤተሰቡን ለመርዳት መዘጋጀቱን ገልጿል።

ቀደም ሲል የስራ እድል ከተፈጠረላቸው የአምቦ ከተማ  ነዋሪ መካከል ወጣት ሰኚ ጉርሜሳ በሰጠው አስተያየት መንግስት ባመቻቸለት የስራ እድል ከቤተሰብ ጥገኝነት ተላቆ ራሱን ከመቻል ባሻገር ሌሎችን ማገዝ መጀመሩን ገልጿል ።

ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን የከፈቱት ስጋ ቤት ለሌሎች 10 ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩንም ወጣት ሰኚ ተናግሯል ።

መንግስት ባመቻቸው ብድር የእንጨትና ብረታ ብረት ስራ ባለቤት መሆኑን የተናገረው ደግሞ የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወጣት ነጋሰ አበበ ነው፡፡

በተሰማራበት የስራ መስክ ውጤታማ በመሆኑ  በአሁኑ ጊዜ ባለሶስት እግር  የእቃ መጫኛ ባጃጅ በመግዛት በየቀኑ ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ደስተኛ ህይወት እየመራ እንደሚገኝ አስረድቷል ።

በአነስተኛ የብድር ገንዘብ ተጠቅሞ በእንጨት ስራ ላይ የተሰማራው የሊበን ጃዊ ወረዳ ወጣት ጀቤሳ ሰፈራ ዛሬ ላይ ለአምስት ሰዎች የስራ እድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ የመኖሪያ ቤት ሰርቶ በማከራየት ተጨማሪ ገቢ እያገኘ መሆኑን ተናግሯል ፡፡

በሚያገኘው ገቢ በትምህርቱ ራሱን ለማሻሻል በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ቅዳሜና እሁድ  በኢኮኖሚክስ የመጀመሪ ድግሪ ትምህርት እየተከታተልኩኝ ነው ብሏል ።

በዞኑ እስከ በጀት አመቱ መጨረሻ 25 ሺህ 877 ስራአጥ ወጣቶችን በ4 ሺህ ማህበራት አደራጅቶ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም