አኩሪ አተር በምርት ገበያ ብቻ እንዲገበያይ ተወሰነ

328

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2011 አኩሪ አተር በአስገዳጅነት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ብቻ እንዲገበያይ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ወሰነ።

በዚህም መሰረት በአንድ ቀን አንድ ሺህ 42 ኩንታል አኩሪ አተር ወደ ምርት ገበያው መጋዘን መግባቱን ለኢዜአ አስታውቋል።

ከአኩሪ አተር በተጨማሪ ቀደም ሲል በአማራጭነት የነበረው አረንጓዴ ማሾ በአስገዳጅነት በምርት ገበያው ብቻ እንዲገበያይ ተወስኗል።

ከታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ/ም ጀምሮ አኩሪ አተርና ሽንብራ ወደ ምርት ገበያው እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን ሽንብራው በአስገዳጅነት ሳይሆን በአማራጭነት የቀረበ ነው።

ግብይቱ በምርት ገበያው ብቻ መካሄዱ የጥራጥሬ ምርቶችን በጥራትና በመጠን በማቅረብ የውጭ ምንዛሪን የሚያሳድግና ለአቅራቢው ተገቢው ዋጋ እንዲከፈለው የሚያችል መሆኑ ተገልጿል።

የአስገዳጅነት ውሳኔው የተሰጠው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የጥራጥሬ ምርቶች ግብይትን አስመልክቶ በቁጥር 377/2008 በወጣው ደንብና በማስፈጸሚያ መመሪያ ቁጥር 010/2009 መሰረት ነው።

ውሳኔው ቡና፣ ሰሊጥና ነጭ ቦሎቄን ጨምሮ አምስት ምርቶች በምርት ገበያው ብቻ እንዲገበያዩ ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በዚህ ወር 39 ሺህ 240 ቶን ሰሊጥ፣ 27 ሺህ 773 ቶን ቡና እና 10 ሺህ 995 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር አገበያይቷል።