በመኮይ ወረዳ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ተያዙ

72

ጋምቤላ  ታህሳስ 26/2011 በጋምቤላ ክልል መኮይ ወረዳ 27 ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን ከአንድ ተጠርጣሪ ጋር ትናንት ምሽት መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳይመን ቲያች ዛሬ ለኢዜአ እንዳሉት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎቹ የተያዙት ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት በአንድ ግለሰብ ቤት ውስጥ ባደረገው ፍተሻ ነው፡፡

የተያዙት እነዚህ የጦር መሳሪዎች  26 ክላሺንኮቭና  አንድ  የብሬን ጠመንጃ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ፖሊስ በአሁኑ ወቅት በተጠርጣሪው ግለሰብ ላይ ምርመራ እየተደረገ  እንደሚገኝ ጠቁመው ሂደቱ እንደተጠናቀቀ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ አስታውቀዋል፡፡

ክልሉ ከደቡብ ሱዳን  ጋር ሰፊ ድንበር ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የህገ ወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውር እየተበራከተ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ችግሩን ለመከላከል ህብረተሰቡን ያሳተፉ የመከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊትም በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ተይዘው እንደነበር ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም