የጋምቤላ ክልል የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ጥናት የተቀናጀ ልማትን ለማካሄድ ያስችላል

68

ጋምቤላ ታህሳስ 25/2011 የጋምቤላ ክልል የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ጥናት የተቀናጀ ልማትን ለማካሄድ ከሚኖረው ፋይዳ ባለፈ ያልተገባ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን ለማስቀረት ጠቀሜታ እንዳለው ተጠቆመ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ቀንድ የአካባቢ ማዕከልና ኔትወረክ ተቋም የተካሄደው የክልሉ መሬት አጠቀቀምና አያያዝ ጥናት የመጨረሻ ረቂቅ ሰነድ ትናንት ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በተቋሙ የጥናቱ አስተባበሪ ዶክተር አዘነ በቀለ ጥናቱን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ጥናቱ በክልሉ ያለውን ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት በተቀናጀ መልኩ ለማልማትና በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያስችል ነው።

የመሬት ሀብትን ባልተጠና መልኩ መጠቀም የብዝሃ ህይወት መመናመንን፣ የአካባቢ መራቆት፣ የአየር መዛባትንና ሌሎችንም ችግሮች እንደሚስከትል ተናግረዋል።

በመሆኑም ጥናቱ በክልሉ ያለውን ሰፊ የእንስሳት፣ የውሃ፣ የደን፣ የዓሣና ሌሎችን ሀብቶች በተቀናጀ መልኩ በማልማት ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ጥናቱ ያልተገባ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና ብክነትን በማስቀረት ረገድም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ነው ዶክተር ዘነበ የጠቆሙት።

እንደእርሳቸው ገለጻ የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ጥናቱ ከፍተኛ የሥራ እድልን፣ የሃብት ግኝትን፣ የአካባቢ ጥበቃን የሚያረጋግጥና በውስጡም 135 ፕሮጀክቶች የያዘ ነው።

በመሆኑም ጥናቱን ፈጥኖ ወደተግባር ምዕራፍ በማስገባት ካልተሰራ የሚፈለገው ውጤት ስለማይገኝ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባ ዶክተር አዘነ ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ "ጥናቱ የክልሉን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በዘመናዊ መልኩ አልምቶ ለመጠቀም የሚያስችል ነው" ብለዋል።

በተጨማሪ በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ለመጠበቅና ለማልማት ጥናቱ ጉልህ ሚና ስላለው ለጥናቱ ተግባራዊነት የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢና ኔትወርክ ተቋም በክልሉ መሬት ሀብት ላይ ጥናት በማካሄድ ልማቱን ለማገዝ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅረበዋል።

ቀደም ሲል በክልሉ ግልጽ የሆነ የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ፖሊሲ ባለመኖሩ ሀብቱ በአግባቡ ሳይለማና ህዝቡም ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን የገለጹት ደግሞ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ ናቸው።

"ጥናቱ ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን በማስቀረት ሀብቱን በአገባቡ በማልማት ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል" ብለዋል።

በረቂቅ ጥናቱ ላይ የክልሉ የካቢኔ አባላት ተወያይተው መጠነኛ ማስተካከያ እንዲደረግበት ሃሳብ የሰጡ ሲሆን በክልሉ ምክር ቤት ጸድቆ ሥራ ላይ እንደሚውልም ተገልጿል።

የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ጥናቱ ለቀጣይ 20 ዓመታት እንዲያገለግል ተደረጎ መዘጋጀቱም በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም