በባሌ ዞን ህጻናትን ከፖሊዮ በሽታ ለመከላከል ክትባት እየተሰጠ ነው

380

ጎባ ታህሳስ 25/2011 በባሌ ዞን ከአምስት ዓመት በታች ዕድሜ ላላቸው 310 ሺህ 200  ህጻናትን  ከፖሊዮ በሽታ ለመከላከል የቤት ለቤት   ክትባት እየተሰጠ ነው፡፡

የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ እሸቱ ቶሎሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ክትባቱ ከዛሬ  ጀምሮ ለአራት ቀናት በ20 ወረዳዎች ላይ ይሰጣል፡፡

በክትባት ዘመቻው ከ2 ሺህ የሚበልጡ ባለሙያዎች፣ ተቆጣጣሪዎችና መንገድ መሪዎች ይሳተፋሉ ።

“በየደረጃው በሚገኙ የጤና ተቋማትና ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ የክትባት አገልግሎቱን ተደራሽ ይደረጋል” ብለዋል ።

 እንደ ኃላፊው ገለጻ የክትባቱ ዓላማ  ከጎረቤት ሀገራት  ወደ ሀገር ውስጥ በድንበር አካባቢ ሊገባ  የሚችለውን  የልጅነት ልምሻ በሽታ አስቀድሞ ለመከላከል ነው፡፡

ለክትባቱ የሚያስፈልገው ቁሳቁስና የሰው ሃይል በሁሉም ቦታ መሟላቱን ጠቁመው  ህብረተሰቡም  ልጆቹን በወቅቱ በማስከተብ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከክትባቱ በተጓዳኝ  በዞኑ የላንቃ መሰንጠቅና የፌስቱላ በሽታ ተጠቂ  የሆኑ ህፃናትና ሴቶችን ቤት ለቤት በሚደረገው ዘመቻ በመለየት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረገል ተብሏል፡፡

በዞኑ የክትባት ዘመቻውን ለመቆጣጠርና ድጋፍ ለማድረግ የተገኙት በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የክትባት አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዮሃንስ ላቀው በበኩላቸው ” የፖሊዮ መከላከያ ክትባት የጎረቤት አገር ሶማሊያን በሚያዋስኑ ባሌ፤ ቦረናና ምስራቅ ሀረርጌ ዞኖች በዘመቻ  ይሰጣል” ብለዋል፡፡

ለፕሮግራሙ ስኬት የዓለም ጤና ድርጅት ጨምሮ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት የመድኃኒትና ተጓዳኝ ድጋፍ አድርገዋል ።

 በጎባ ከተማ ምዕራብ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አሽረቃ ሱልጣን  በሰጡት አስተያየት ” በየጊዜው በሚሰጠው የክትባት አገልግሎት ልጆቼን  ከበሽታ መከላከል ችያለሁ ” ብለዋል፡፡

በአሁኑ ዙርም ክትባት እንደሚሰጥ አስቀድሞ ስለተነገረን ልጆቻችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ  መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

መንግስት በነጻ የሚሰጠው የክትባት አገልግሎት ልጆቻቸውን ከበሽታው ስጋት ነፃ እንዳደረጋቸው የገለጹት ደግሞ ሌላዋ የከተማው  ነዋሪ ወይዘሮ በቀለች ተሰማ ናቸው፡፡

“በአካባቢያችን አስቀድሞ የተደራጀው የሴቶች  ልማት ቡድን  ክትባትን ጨምሮ ሌሎች ፕሮግራሞች ሲኖሩ በግንባር ቀደምትነት እንድንሳተፍ እድል እየሰጠን ነው “ብለዋል፡፡

በባሌ ዞን ከሚኖረው አንድ ሚሊዮን 800ሺህ  ህዝብ ውስጥ  ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት 16 ነጥብ 4 በመቶውን ይሸፍናሉ ተብሎ እንደሚገመት ከዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ  ያመለክታል፡፡