አንድነታቸውን እንደሚያጠናክሩ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ

685

ነቀምትታህሳስ 25/2011 አንድነታቸውን በማጠናከር የመጡለትን ዓላማ ለማሳካት እንደሚተጉ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸውን የሰጡ ተማሪዎች ገለጹ።

ዩኒቨርስቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማሩን ስራ ማጠናከር በሚቻልበት ዙሪያ ለተማሪዎች ያዘጋጀው የሁለት ቀናት ስልጠና በነቀምት ከተማ ተካሄዷል፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የዩኒቨርሲቲው የሶስተኛ ዓመት ተማሪ አስናቀ ወርቁ እንዳለው  ሥልጠናው የተማሪዎችን አንድነትን በማጠናከር ረገድ ገንቢ አስተዋጽኦ አለው፡፡

በተለይ ካለምንም ስጋት ነፃ ሆኖ ትምህርቱን ለመከታተል ስልጠናው መነሳሳት እንደፈጠረለት ተናግሯል።

ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ቤተሰቦቻቸው የሄዱ ተማሪዎች በአስቸኳይ ወደ ትምህርት ገበታቸው በመመለስ በትምህርታቸው እንዲተጉ መክሯል ።

ሌላዋ የሶስተኛ ዓመት የኢኮኖሚክስ ተማሪ ዝናሽ ባህሬ በበኩሏ በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው ሠላም መኖሩንና  እስካሁንም የተፈጠረ ችግር እንደሌለ ገልጻለች።

በስጋት ተነሳስተው ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ቤተሰባቸው የሄዱ ተማሪዎች ዛሬ ነገ ሳይሉ መመለስ እንዳለባቸው ጠቅሳ በተለይ ሥልጠናው የተማሪዎችን አንድነትና ህብረት ከማጠናከር ባለፈ ራዕያቸውን ለማሳካት እንደሚረዳ ተናግራለች።

መድረኩ ከፍርሃት በመላቀቅ ትምህርቷ ላይ ብቻ እንድታተኮር እምነት እንዳሳደረባት የገለጸችው ደግሞ የሶስተኛ ዓመት የሎጀስቲክ ተማሪ አዲሴ ብርሃኑ ናት።

ተማሪ አዱኛ አየለ በበኩሉ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ተማሪዎች  በመፈቃቀርና በወንድማዊነት በመተሳሰብ ትምህርታቸውን ከዳር ለማድረስ ስልጠናው አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል።

” በተለይ ተማሪ የመጣበትን  ዓላማ እንዳያሳካ ከሚያደነጋግሩ የማህበራዊ ሚዲያ   አሉባልታ በመራቅ ትምህርታችን ላይ ብቻ ልናተኩር ይገባል ” ብሏል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ናቶ በላቸው በአከባቢው ከሚገኙ ቄሮዎች፣የሃገር ሽማግሌዎችና ከኃይማኖት አባቶች ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ በዩኒቨርሲቲው ችግር እንዳይከሰት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጿል።

ዩኒቨርሲቲዎች የእውቀት አውድማ እንጂ ተማሪዎች በስጋት የሚንቀሳቀሱበትና ከመተባበር ይልቅ  የሚጠፋፉበት እንዳልሆነ የተናገሩት ደግሞ በስልጠናው መድረክ የተገኙት የኦሮሚያ ካቢኔ አባል ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ ናቸው፡፡

ለሀገርና ለወገን የሚበጅ ዕውቀት የሚገበዩበት፣በጥበብ የሚራመዱበት እንጂ መከፋፈልን ፣ዘረኝነትን፣የሰፈርንና የመንደርተኝነት ዕይታ በማንገብ ጊዜያቸውን በከንቱ የሚያባክኑበት እንዳልሆነም አስረድተዋል።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተመስጌን ጋሮማ በበኩላቸው  በዩኒቨርሲቲው በተማሪዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዳለ ገልጸው “እስካሁንም የተከሰተ ችግር የለም” ብለዋል።

በቅርቡ በምዕራብ ኦሮሚያ ተፈጥሮ ከነበረው የስራ ማቆም  ጋር በተያያዘ ለአንድ ሳምንት ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማሩ ሥራም በግምቢ ካምፓስ መጀመሩን አመልክተዋል።

በዋና ግቢውም የሁለተኛ ዲግሪ  መርሃ ግብሩ መቀጠሉንና የሌሎችም የትምህርት ፕሮግራሞች ስልጠናው ማብቃቱን ተከትሎ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

የባከነውን የትምህርት ክፍለ ጊዜ በቅዳሜና እሁድ እንዲሁም በማታው ፕሮግራም  በማካካስ ተማሪዎችን ለማብቃት በዩኒቨርሲቲው  ሰኔት መወሰኑንም ዶክተር ተመስጌን አብራርተዋል።