”ህይወት አድን ተግባር”

2031

”ህይወት አድን ተግባር”  ምናሴ ያደሳ(ኢዜአ)

ወይዘሮ ቆንጂት ወልደማርያም በመቱ ካርል ሪፈራል ሆስፒታል እናቶችና ህጻናት ክፍል ነው ያገኘኋቸው፡፡ ወንድ ልጅ ተገላግለው ከልጃቸው ጋር በክፍሉ ተኝተዋል፡፡ ከአጠገባቸው ቆመው የሚያስታምሟቸው ባለቤታቸው አቶ አለማየሁ ኢረና  ፊት ላይ ግን የደስታም የጭንቀትም ስሜት ይስተዋላል፡፡

ቀረብ ብዬ ከአንደበታቸው እንደተረዳሁት የደስታ ስሜቱ ከባለቤታቸው የልጅ ገፀ በረከት ስላገኙ  ፣ ጭንቀቱ ደግሞ በወሊድ ወቅት ከፍተኛ ደም ስለፈሰሳቸው በህይወት ለመቆየት ሌላ ተተኪ  ደም እንደሚያስፈልጋቸው  ስለተነገራቸው ነው፡፡

በፊታቸው ላይ ይታይ የነበረው የተደበላለቀ ስሜት ግን ብዙም ቆይታ አልነበረውም፡፡ ከሆስፒታሉ ባለሙያዎች የተነገራቸው ብስራት የተደበላለቀውን ስሜት ወደ ደስታ ቀይሮታል፡፡ በሆስፒታሉ በቂ ተተኪ ደም በመኖሩ ባለቤታቸው ያለ ምንም ክፍያ  እንደሚያገኙ ተነግሮአቸው ነው ።

“በህይወት ለመቆየት ሌላ ተተኪ ደም እንደሚያስፈልጋት ሲነገረኝ በጣም ተጨንቄ ነበር “ የሚሉት አቶ አለማየሁ አሁን  ከሆስፒታሉ በነጻ እንደሚሰጣቸው ስላወቁ  ሸክሙና ጭንቀቱ ሁሉ ተቃሎላቸው በደስታ ስሜት እንደተዋጡ ነገሩኝ፡፡

በደም እጥረት የሰው ህይወት  ሊያልፍ እንደሚችል ግንዛቤ ቢኖራቸውም ስለ በጎ ፈቃደኝነት ደም ልገሳና ጠቀሜታው በዝርዝር የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ይናገራሉ፡፡

ሰብአዊነት ከሚሰማቸው ግለሰቦች በበጎ ፈቃድ የተለገሰ ደም ባለቤታቸውን ማዳኑ እሳቸውም በፈቃደኝነት በመለገስ የሌላውን ህይወት ለማዳን እንዳነሳሳቸው ይናገራሉ፡፡ “ከአሁን በኋላ እኔም የሌላውን ህይወት ለማዳን የሚጠበቅብኝን ማድረግ አለብኝ የምለው ብድር ለመክፈል አይደለም” ያሉት አቶ አለማየሁ ይልቁንም ደግነትና ሰብአዊነትን ስላስተማራቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ደም የማይለግሰው ሰብአዊነት ከማጣት ወይም ከንፉግነት አይደለም፡፡ እንደ አቶ አለማየሁ ያሉት ጠቀሜታውንና አስፈላጊነቱን በደምብ ባለመረዳታቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ ደም መስጠት በጤና ላይ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል ከሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በመነሳት ነው፡፡

በመቱ ከተማ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ሬድዋን መሀመድም ይሄንኑ ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡ “ከሁለት አመታት በፊት ስለ ደም መለገስ ጠቀሜታ ምንም ግንዛቤ አል ነበረኝም” ያሉት አቶ ሬድዋን ካለፈው አመት አንስቶ ደም መለገስ በደም እጦት ሊያልፍ የሚችለውን ህይወት እንደሚያድንና በግል ጤናም ጠቀሜታ እንዳለው ባገኙት ግንዛቤ በፈቃደኝነት መለገስ እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡

ግንዛቤ በማዳበር ደም መለገስ ከጀመሩ ወዲህ ቢያንስ ሶስት ሰዎች ማስተማራቸውንና ደም እንዲሰጡ ማድረጋቸውን ነው የገለጹት፡፡ በዚህ አመትም አንድ ግዜ  እንደለገሱ ነው የሚናገሩት፡፡

ደም መለገስ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት መታደግ እንደሚችል በተግባር ማየታቸው እንዲሁም ግንዛቤ ያዳበሩ ግለሰቦች ለሌላው በሚሰጡት ትምህርት የደም ለጋሾች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንዲመጣ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡

የደም ባንክ በኢትዮጵያ ከተቋቋመ 50 አመታት ያክል ቢያስቆጥርም እስካሁን በበጎ ፈቃድ የደም ልገሳ ዙርያ ለህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ባለመሰጠቱ የደም ለጋሾች ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡ በአለም ጤና ድርጅት መስፈርት ከአንድ ሀገር ህዝብ ቢያንስ አንድ ከመቶ ያህሉ በየአመቱ ደም መለገስ አለበት፡፡

በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ካላት አንድ መቶ ሚሊዮን ያህል ህዝብም ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ያህሉ በየአመቱ ደም መለገስ ቢኖርበትም በአሁኑ ወቅት የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥር ከ175 ሺህ አይበልጥም፡፡ ይህም በመስኩ ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ አመላካች ነው፡፡

የመቱ ደም ባንክ ማዕከል በአካባቢው ከተቋቋመ ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማዳበር የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥር እንዲበራከት በዋነኛነት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት የነበረ መሆኑን ከማዕከሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የማዕከል ስራ አስከያጅ አቶ ድሪባ ገመቹ እንዳሉት ማዕከሉ በአካባቢው እንደተቋቋመ እንደ ትልቅ ተግዳሮት ሲታይ የነበረው በመስኩ የህብረተሰቡ ግንዛቤ ያለመዳበር ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ በመጀመርያዎቹ ሁለት አመታት ደም ለማሰባሰብ ተቸግሮ እንደነበረ ነው የሚናገሩት፡፡

ማዕከሉ አገልግሎት በሚሰጥባቸው የኢሉአባቦር እና ቡኖ በደሌ ዞኖች እንዲሁም በደቡብ ክልል ሸካ ዞን የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማዳበር በትምህርት ቤቶች፣ በመንግስት መስርያ ቤቶች በተለያዩ ማህበራዊ አደረጃጀቶችና በመሳሰሉት አካባቢዎች በተሰጡት ትምህርቶች በፈቃደኝነት ደም የሚለግሱ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር ተደርጓል፡፡

ባለፉት አምስት ወራትም በአካባቢዎቹ የሚገኙ 1ሺ950 ሰዎች በፈቃደኝነት ቀርበው ደም ለግሰዋል፡፡ ይህም ባለፈው አመት የመጀመሪያ ግማሽ አመት በፈቃደኝነት ከለገሱት ከ750 በላይ ብልጫ አለው ብለዋል፡፡እስከ ያዝነው አመት መጨረሻም ከ5ሺ ዩኒት በላይ ደም ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

ማዕከሉ የሚያሰባስበውን ደም በአካባቢው ለሚገኙ የመቱ ካርል ሪፈራል ሆስፒታል፣ ለበደሌ፣ዳሪሙና ደምቢ ሆስፒታሎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ሸካ ዞን ለቴፒ ሆስፒታል በነጻ እያቀረበ ነው፡፡

ማዕከሉ በአካባቢው ከመቋቋሙ በፊት በነዚህ ሆስፒታሎች በደም እጥረት የተነሳ የሰው ህይወት ሲያልፍ ነበር” የሚሉት አቶ ዲሪባ  በአሁኑ ወቅት በቂ ደም ለሆስፒታሎቹ ከማዳረስ ባለፈ ለሌሎች የአካባቢው  ሆስፒታሎችም እስከ ማቅረብ መድረሳቸውን ይገልጻሉ፡፡

በቋሚነት ደም ከሚያቀርብባቸው ከእነዚህ ሆስፒታሎች በተጨማሪም ዘንድሮ ተጨማሪ ደም ላስፈለጋቸው የጅማ ፣ነቀምቴና ጋምቤላ ሆስፒታሎች 311 ዩኒት ደም ማቅረቡን አቶ ዲሪባ ተናግረዋል፡፡

የመቱ ደም ባንክ ማዕከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የጤና ተቋማቱን ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ የደም አሰባሰብና አያያዙን የአለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት በመከወን  ውጤታማ ተግባራት ተገኝቷል፡፡

በአለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት ደም ተገቢ በሆነ መያዣ በመያዝና ከተለያዩ በሽታዎች ነጻ መሆኑን ደረጃውን በጠበቀ መሳርያ በመመርመር ከሚሰበሰበው ደም ከ90 እስከ 95 በመቶ የሚሆነውን ተጠቃሚው ጋ ማድረስ እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡ አቶ ድሪባ እንዳሉት ማዕከሉ በዚህ አመት ካሰባሰበው ደም ከ95 ከመቶ በላይ የሚሆነው ንጹህ በመሆኑ ተጠቃሚ ጋር ማድረስ ተችሏል፡፡ ይህም የአለም ጤና ድርጅት መስፈርት ያሟላ ነው፡፡

ከበጎ ፈቃደኞች የሚሰበሰበው ደም ተጠቃሚው ጋር ሳይደርስ ከሚጣልባቸው ምክንያቶች መካከል ከምርመራ በፊት ሲሰበሰብ በተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች የተበከለ መሆኑ፣ የሚሰበሰበው ደም  በሚሰበሰብበት መሳርያ ውስጥ የሚገኝ ኬሚካል ከሚፈልገው በላይ ወይም በታች ሲሆን እንዲሁም በደም መያዣ እቃዎች የቅዝቃዜ መጠን አነስተኛ ወይም ከፍተኛ መሆን ይጠቀሳሉ፡፡

ማዕከሉ በዚህ አመት ከበጎ ፈቃደኞቹ ካሰባሰበው 1ሺህ 950 ዩኒት ደም ውስጥ ተጠቃሚው ጋር ሳይደርስ የተጣለውም 5 ከመቶ ያህሉ ነው፡፡  የብክነት መጠኑን አነስተኛ ማድረግ የተቻለው ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ በደም የሚተላለፉ በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች እንዳይለግሱ በመደረጉና  በበቂ ባለሙያዎች በደም አያያዝ እና ምርመራ ዙርያ ስራዎች በመሰራታቸው ነው ይላሉ፡፡

በማዕከሉ ውስጥ ለደም ምርመራ ጥቅም ላይ የሚውሉ የመመርመርያ መሳርያዎችም  በአለም አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ የሚውሉና ዘመናዊ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት፡፡ በተለይም ከዚህ ቀደም በኤች አይቪ ቫይረስ ምርመራ ቫይረሱ በደሙ ውስጥ መኖር እና ያለመኖሩን ለማወቅ ሶስት ወር ያህል መጠበቅ ይጠይቃል፡፡ አሁን ግን እጅግ ዘመናዊ የሆነ መሳርያ በመጠቀም በአንድ ቀን ውስጥ ቫይረሱ መኖር ያለመኖሩን ማወቅ እንደሚቻል ነው የተናገሩት፡፡

በመቱ ካርል ሆስፒታል የላቦራቶሪ ክፍል ባለሙያ አቶ ብርሀኑ አመና እንዳሉት የመቱ ደም ባንክ ማዕከል ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች በማሰባሰብ ለሆፒታሉ ደም ማቅረብ ከጀመረ ወዲህ በደም እጦት ህይወቱ የሚያልፍ ታካሚ ዬለም፡፡ ሆስፒታሉ ከማዕከሉ የሚያገኘውን ደም ክሮስ ቼክ ከሰራ በኋላ ተተኪ ደም ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች በነጻ ይሰጣል፡፡

ከዚህ ቀደም ተተኪ ደም የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች  በግዢ አልያም በቤተሰብ ልገሳ ያገኙ ነበር” ያሉት አቶ ብርሀኑ ይህም በአነስተኛ የኢኮኖሚ አቅም ላላቸው ታካሚዎች እጅግ ከባድ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ በግዢ የሚገኘው አልያም በቤተሰብ ልገሳ የሚቀርበው ተተኪ ደም  ከለጋሹ የሚወሰደው ታካሚው ተተኪ ደም እንደሚያስፈልገው ከተነገረው በኋላ በመሆኑ በወቅቱ ሳይደርስላቸው  ህይወቱ የሚያልፍ ታካሚ እንደነበረም ይናገራሉ፡፡

በመቱ የደም ባንክ ማዕከል ለህብረተሰቡ እየተሰጠ ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና  የበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች ቁጥር እያደገ መምጣት የበጎ ፈቃድ ደም ልገሳ ባህሉ በሚፈለገው ደረጃ እንዲደርስ ተስፋ የሚጣልበት ነው፡፡ ይህም በሌሎች አካባቢዎች እንደ ልምድ ተወስዶ ሊሰራበት የሚገባ ተግባር ነው እንላለን፡፡ ህብረተሰቡ ደም ልገሳ ህይወት አድን በጎ ተግባር መሆኑን ተረድቶ በመደበኛነት  እስኪለግስ ድረስ ትምህርቶች ሊሰጡ ይገባል፡፡

ደም መለገስ ሰጪውንም ተቀባዩንም የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ እንዳልሆነ ማህበረሰቡ በሚገባ መገንዘብ አለበት፡፡ ደም መለገስ ማለት ልትቋረጥ የተቃረበችን ህይወት መልሶ  ማለምለም ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለጋሾች በጤናቸው ከሚያገኙት ጥቅም ባለፈ  ትልቅ የአዕምሮ እርካታ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡

የለጋሾችን ቁጥር ከማሳደግ ጎን ለጎንም  በጤና እና በተለያዩ ምክንያቶች ደም መለገስ የሌለባቸው እንዳይለግሱ ትምህርት መስጠት ይገባል፡፡ ይህም ከሚሰበሰበው ደም ተጠቃሚው ጋር ሳይደርስ የሚባክነውን መጠን ለመቀነስ ይረዳል፡፡