በምስራቅ ጎጃም ዞን የጤና መድን አገልግሎት በከተሞች እየተተገበረ ነው

914

ደብረማርቆስ ታህሳስ 25/2011 የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት በምስራቅ ጎጃም ዞን  ከገጠር ወደ ከተሞች በማስፋፋት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ ገጠር አካባቢዎች አንድ ሚሊዮን 700 ሺህ ያህል ሰዎች  የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

በመምሪያው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አስተባበሪ አቶ ላቃቸው አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት ዓላማው  ነዋሪዎች አንድ ጊዜ በመፈጽሙት  አነስተኛ ክፍያ በዓመቱ ውስጥ  በመንግስት የጤና ተቋማት ሁሉ አቀፍ የህክምና አገልግሎት  ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው፡፡

በዞኑ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮም በ16 የገጠር ወረዳዎች ሲከናወን የቆየው የጤና  መድን አገልግሎተ ካለፈው ዓመት አጋማሽ አንስቶ  በከተሞች እየተተገበረ ይገኛል።

እስካሁን 14 ሺህ የከተማ ነዋሪዎችን  የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባል በማድረግ የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እንደ ጀመሩ አስተባባሪው አመልክተዋል፡፡

ተጠቃሚ መሆን የጀመሩት በደብረማርቆስ፣ ሞጣ፣ ቢቸናና ደጀን ከተማ አስተዳደሮች  የሚገኙ ነዋሪዎች ናቸው፡፡

አንድ ሰው እንደ ገቢ አቅሙ አነሰተኛው 450 ብር ከፍተኛው ደግሞ 1ሺህ 200 ብር በመክፈል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ይችላል፡፡

አስተባባሪው እንዳሉት እስካሁን ተመዝግበው  የጤና መድን አባል ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችም የጤና ችግር ሲያጋጥማቸው በጤና ተቋማቱ  መታከም የሚችሉበት ካርድ ተሰጥቷል።

አገልግሎቱን በማስፋፋት እስከ ዓመቱም  መጨረሻም የአባላትን ቁጥር 20 ሺህ ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ  መሆኑም ተመልክቷል።

በደብረማርቆስ ከተማ  የቀበሌ ሁለት  ነዋሪ ወይዘሮ ረድኤት ተመስገን በሰጡት አስተያየት”  የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባል መሆኔ ለወደፊት በጤናዬ  ላይ ችግር ቢገጥመኝ ያለምንም የገንዘብ እጥረት እንድታከም ያስችለኛል” ብለዋል።

የጤና መድን አባል መሆናቸው እራሳቸውም ሆነ ቤተሰባቸው  ቢታመም  አንዴ  በፈጸሙት ክፍያ  በመንግስት  የጤና ተቋም  መገልገል የሚችሉበት ካርድ ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ በዚሁ ከተማ የቀበሌ አራት  ነዋሪ አቶ ሀብቴ ልቅናው ናቸው፡፡

በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተደረገ እንቅስቃሴ የከተማን ሳይጨምር በገጠር አከባቢዎች   አንድ ሚሊዮን 700 ሺህ ያህል ሰዎች  የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባል በመሆን በአገልግሎቱ እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ከዞኑ ጤና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡