በቂ የሕክምና ክትትል አለማድረግ ጨቅላ ህጻናትን ለአተነፋፈስ ችግር እያጋለጠ ነው….አንድ ጥናት

921

አክሱም ታህሳስ 25/2011 በእርግዝናና በወሊድ ወቅት በቂ የሕክምና ክትትል አለማድረግ ጨቅላ ህጻናትን ለአተነፋፈስ ችግር እያጋለጠ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።

የተለያዩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች የቀረቡበት ኮንፈረንስ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።

በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ጤና ሳይንስ መምህር ሓጎስ ጣሰው በወሊድ ወቅት በጨቅላ ህጻናት ላይ የሚከሰተውን የአተነፋፈስ ችግር መንስኤ አስመልክተው ያካሄዱትን ጥናት አቅርበዋል።

መምህሩ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት በወሊድ ወቅት በቂ የሕክምና ክትትል አለማድረግ ጨቅላ ህጻናትን ለአተነፋፈስ ችግር እያጋለጠ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደረገ ጥናት ከ130 ሚሊዮን ጨቅላ ውስጥ ህጻናት 4 ሚሊዮን ያህሉ  በአተነፋፈስ ችግር ምክንያት ለህልፈት እንደሚዳረጉ አመለክተዋል።

በትግራይ ማዕከላዊ ዞን በሚገኙ አራት የመንግስት አጠቃላይ ሆስፒታሎቹ አዲስ በተወለዱ 176 ጨቅላ ህጻናት ላይ ለአምስት ወር ባካሄዱት ጥናትም ተመሳሳይ ችግር በ88 ህጻናት ላይ ተከስቶ እንደነበር ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ደም መፍሰስ፣ ክብደት መቀነስና ያለዕድሜ መወለድ የችግሩ መንስኤዎች መሆናቸውንም በጥናቱ ማረጋገጣቸው ነው የገለጹት፡፡

በእርግዝናና በወሊድ ወቅት በቂ የሕክምና ክትትል አለማድረግ የችግሩ ምንጭ መሆኑን የገለጹት መምህር ሓጎስ፣ በወሊድ ጊዜ ከአተነፋፈስ ችግር ጋር ተያይዞ በጨቅላ ህጻናት ላይ ሊከሰት የሚችለውን የሞት አደጋ ማስቀረት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት በተለይ የእናቶች ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ የጠቆሙት መምህሩ የህጸናትን ህይወት ለመታደግ በስርአተ ጾታ፣ በጤና አክስቴንሽንና በስርአተ ትምህርት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአክሱም ቅድስተ ማርያም ሆስፒታል አዋላጅ የሆኑት ሲስተር ተከዘ ግደይ በበኩላቸው  በሆስፒታሉ በወር በአማካይ ከሚወለዱ 100 ህጻናት ውስጥ 4 በመቶ ችግሩ እንደሚከሰትባቸው ተናግረዋል፡፡

“እናቶች በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት ተገቢውን የሕክምና ክትትል ከተደረገላቸው ችግሩን በቀላሉ መከላከል ይቻላል” ብለዋል።

እናቶች በጤና ተቋም በባለሙያ ድጋፍ ታግዘው እንዲወልዱ በቀጣይ የማስገንዘብ ሥራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶችና ህጻናት ጤና ባለሙያ ሲስተር ትርሓስ አስመላሽ በበኩላቸው “ በጨቅላ ህጻናት ላይ የሚደርሰውን የአተነፋፈስ ችግር ለመከላከል ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብበር እየሰራ ነው ” ብለዋል።

በየቀበሌው የጤና ልማት ቡድን አባላትና እና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ነፍሰጡር እናቶች በእርግዝና፣ በወሊድና በድህረ ወሊድ ወቅት በጤና ተቋማት ክትትል እንዲያደርጉ ግንዛቤያቸውን የማሳደግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ ችግሩን ለመከላከል በሁሉም ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች የአዋላጅ  ባለሙያዎች እና የህክምና መሳሪያዎች እንዲሟሉ መደረጉን ሲስተር ትርሓስ ተናገረዋል።

በተለይ በወሊድ ጊዜ የሚያጋጥም የህጻናት የአተነፋፈስ ችግርን መከላከል በሚቻልበት መንገድ ላይ ለ21 ቀን ለባለሙያዎች የንድፈ ሀሳብና የትግባር ስልጠና መሰጠቱን ነው ያስረዱት።

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ድህረ ምረቃ ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ በሪሁ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሁለት ዓመታት የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

“በዩኒቨርሲቲው የተካሄደው የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስም ምሁራንና ተመራማሪዎች የልምድ ልውውጥ፣ እውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ ያግዛል” ብለዋል።

የጥናትና ምርምር ውጤቶች ወደ ህዝቡ ወርደው ተግባራዊ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ለህትመት ለማብቃት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በዩኒቨርሲቲው ምሁራን ከተካሄዱ የጥናትና ምርምር ውጤቶች አንዳንዶቹ በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ለህትመት መብቃታቸውንም መምህር ሓጎስ አስታውሰዋል።