ከአውሮፕላን መንደርደሪያ ተንሸራቶ የወጣው አውሮፕላንን ጉዳይ የሚያጣራ ቡድን ወደ ስፍራው ተልኳል

94

አዲስ አበባ ታህሳስ 25/2011 በዩጋንዳ ኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲያርፍ ከአውሮፕላን መንደርደሪያው ተንሸራቶ የወጣው የኢትዮጵያ የአየር መንገድ አውሮፕላን ያጋጠመውን እክል የሚያጣራ የምርመራ ቡድን ወደ ስፍራው መላኩን አየር መንገዱ አስታወቀ።

ዛሬ ማለዳ 139 ተሳፋሪዎችን ይዞ በበረራ ቁጥር  ET 338፣ ቦይንግ  737-800 የበረረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ዩጋንዳ ኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲያርፍ ከአውሮፕላን መንደርደሪያው የተወሰኑ ሜትሮች ተንሸራቶ መውጣቱ ነው የተነገረው።

የአየር መንገዱ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አስራት በጋሻው ከአውሮፕላን መንደርደሪያው ተንሸራቶ የወጣው የአየር መንገዱ አውሮፕላን ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰበት ለኢዜአ ገልጸዋል።

በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት 139 ተሳፋሪዎችና የበረራ ሰራተኞችም ምንም አይነት ጉዳት ሳይገጥማቸው ከአውሮፕላኑ በሰላም መውረዳቸውን ተናግረዋል።

አውሮፕላኑ በአሁኑ ሰአት ከመንደርደሪያው ላይ ተነስቶ ወደ ተርሚናል መግባቱንም አመልክተዋል።

አውሮፕላኑ የገጠመውን እክል የሚመረምር ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የተውጣጣ የደህንነት ቡድን ወደ ስፍራው እያመራ መሆኑንና በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከቀኑ 7 ሰአት ከ45 ደቂቃ እንደሚደርስ ጠቁመዋል።

የምርመራ ቡድኑ ከዩጋንዳ ሲቪል አቪዬሽን ባለሙያዎች ጋር በመሆን በአውሮፕላኑ ላይ ምርመራ በማድረግ ውጤቱን ይፋ እንደሚያደርግም ነው አቶ አስራት ያስረዱት።

ያጋጠመው ችግር ከታወቀ በኋላ አውሮፕላኑ ጥገናና ቁጥጥር (inspection) ተደርጎለት ወደ ስራ እንደሚመለስም አመልክተዋል።

አውሮፕላኑ ወደ ተርሚናል ከገባ በኋላ ሌላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዩጋንዳ ኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተሳፋሪዎችን ይዞ ማረፉን ጠቁመዋል።

አውሮፕላኑ በገጠመው እክል ምክንያት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር እስከ ረፋዱ 4 ሰአት 40 ደቂቃ ድረስ የኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አገልግሎት መስጠት አቁሞ እንደነበረና በአሁኑ ሰአት አየር ማረፊያው ሙሉ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም አስረድተዋል።

ከመንደርደሪያ ተንሸራቶ በወጣው አውሮፕላን ምክንያት በረራቸው ለተስተጓጎለው ተሳፋሪዎች አየር መንገዱ ይቅርታ እንደጠየቀና ወደ አዲስ አበባ ለሚደረገው የመልስ በረራም አማራጭ በረራ እንዳዘጋጀላቸው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም