በአማራ ለ272 ሺህ 400 ልጃገረዶች የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ተሰጠ

923

ባህርዳር ታህሳስ 24/2011 ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው 272 ሺህ 400 ልጃገረዶች የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት መሰጠቱን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።

ክትባቱ ከታህሳስ 1 እስከ 23 ቀን 2011 ዓ.ም የተሰጠ መሆኑ ተነግሯል።

በቢሮው የክትባት ባለሙያ አቶ ዋሴ ይታገስ ለኢዜአ እንደገለጹት ክተባቱ የተሰጠው  በ164 ወረዳዎች ስር በሚገኙ 8 ሺህ 890 ትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማት ነው።

“ይከተባሉ ተብለው በእቅድ ከተያዙ ልጃገረዶች ውስጥ 95 በመቶዎቹ ተከትበዋል” ብለዋል ።

ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ክትባቱ ሙሉ በሙሉ ባልተሰጠባቸው በማዕከላዊ ጎንደር ሁለት ወረዳዎችና በደቡብ ወሎ ወረኢሉ ወረዳ ዘጠኝ ቀበሌዎች ወደፊት የሚሰጥ መሆኑን አመላክተዋል ።

“ክትባቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጣቸው ልጃገረዶችም ከስድስት ወር በኋላ ለሁለተኛ ዙር ክትባቱን ዳግም እንዲወስዱ ይደረጋል ” ብለዋል ።

የማህፀን ጫፍ ካንሰር መንስኤው “ሂውማን ፓፒሎማ” በተባለ ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ ሲሆን እናቶች በበሽታው መያዛቸውን ሳያውቁ እስከ 20 ዓመት ሊቆዩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ልጃገረዶች በለጋነት እድሜያቸው የግብረ ስጋ ግንኙነት መጀመር፣ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ፆታዊ ግንኙነት መፈፀም ለበሽታው ከሚያጋልጡ መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

በባህርዳር ከተማ የአየለች ደገፉ መታሰቢያ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ቢታኒያ አማረ “ክትባቱ ስለሚያስገኘው ጥቅም ቀደም ብየ ከቤተሰቦቼ ግንዛቤ በማግኘቴ  ሳላመነታ ተከትብያለሁ” ብላለች ።

“የበሽታውን አስከፊነትና ሰለ ክትባቱ ጥቅም ከጤና ባለሙያዎች ገለጻ በመረዳቴ ተከትቤያለሁ” ያለችው ደግሞ የሽምብጥ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ኤፍራታ አማረ ናት።