በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ሲያጋጥም የነበረው የጸጥታ ችግር መፈታቱ ተገለጸ

80

አሶሳ ታህሳስ 24/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች ወሰኖች አካባቢ በታጠቁ ኃይሎች ሲያጋጥም የነበረው አለመረጋጋት ወደ ሰላም መመለሱን ችግሩን ለመፍታት የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።

ኮማንድ ፖስቱ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በምዕራብና ምስራቅ ወለጋ፣በቄለምና ሆሮጉድሩ ወለጋ፣በኢሉአባቦራና ቡኖ በደሌ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ካማሺና ማኦኮሞ የታጠቁ ኃይሎች ጥፋት ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

በዚህም ለሰው ህይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ምክንያት ከመሆናቸውም ባለፈ ዜጎችን በማፈናቀልና የአካባቢውን እንቅስቃሴ በመገደብ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መፍጠራቸውን ኮማንድ ፖስቱ አስታውቋል።

ካላፈው ታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም. መግቢያ ጀምሮ ሥራውን በይፋ የጀመረው ኮማንድ ፖስቱ ህብረተሰቡን በጉዳዩ ላይ በማወያየት ለማሳተፍ ጥረት አድርጓል፡፡

አካባቢውን ሲያተራምሱ የነበሩ ህገ-ወጥ ታጣቂ ሃይሎቹ እጃቸውን በሠላም እንዲሰጡ ያደረገ ሲሆን ፈቃደኛ ያልሆኑትን ደግሞ የገቡበት ገብቶ የማያዳግም እርምጃ መውሰዱን አስረድቷል።

በርካታ የጥፋት ሃይሎችን በቁጥጥር ሥር ሲያውል ለጥፋት የሚጠቀሙባቸውን የጦር መሣሪያዎችና በሚሊዮን የሚቆጠር ብር በቁጥጥር ሥር ማዋሉንም ኮማንድ ፖስቱ ገልጿል፡፡

የተወሰደውን እርምጃ ተከትሎ በአሁኑ ወቅት በተጠቀሱት አካባቢዎች ተዘግተው የነበሩ መንዶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ ባንኮች፣ የንግድ ድርጅቶችና ሌሎችም ሙሉ በሙሉ ሥራ ጀምረዋል ብሏል ኮማንድ ፖስቱ፡፡

ህብረተሰቡም ያምንም ሥጋት በአካባቢው በመንቀሳቀስ የዕለት ተዕለት ተግባሩን እያከናወነ መሆኑን አመልክቷል፡፡

በቁጥጥር ሥር የዋሉ ህገ-ወጥ ታጣዊዎችንና የያዟቸውን የጦር መሣሪያዎች፣ ገንዘብና ሌሎችንም የጥፋት ግብዓቶች በጥቂት ቀናት ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግም ኮማንድ ፖስቱ  አስታውቋል፡፡

ኮማንድ ፖስቱ የአካባቢውን ሠላም ለመመለስ ባደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ድጋፍ የማይተካ ሚና እንደተጫወተ ጠቅሶ ይህ እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም