አንድነት እንዲጠናከር የኦርቶዶክስ ካህናት በትጋት እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ

126

አሶሳ ታህሳስ 24/2011 በሀገሪቱ ግጭት ተወግዶ አንድነት እንዲጠናከር  ካህናት ተግተው በመስራት የድርሻቸውን እንዲወጡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ሩፋኤል ጥሪ አቀረቡ፡፡  

ቤተ-ክርስቲያኗ በአሶሳ ሀገረ ስብከት ለሚገኙ የኃይማኖቱ መሪዎችና ምዕመናን የሠላምና የእርቅ ስልጠና አካሂዳለች፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ፣  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የጋምቤላ፣ የምዕራብ ወለጋ እና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ሩፋኤል በስልጠናው ወቅት  እንደተናገሩት የተለያዩ ኃይማኖቶችን በመከተል አብሮ መኖር የኢትዮጵያዊያን ዋነኛ እሴት ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን  ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ በወንድማማች ህዝቦች መካከል ጠብ የሚዘሩአካላት እየታዩ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ፈጣሪ ከሚጠላቸው ሐጢያቶች መካከል አንዱ እና ዋነኛው  ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ አሶሳን ጨምሮ በሀገሪቱ 52 ሀገረ  ስብከቶች የሚሰጠው የዚሁ ስልጠና ዓላማ ወጣቱ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለጥፋት እንዳይጋለጥ ካህናት የማስተማር ኃላፊነታቸውን  እንዲወጡ ለማሳሰብ ነው ሲሉ ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ሩፋኤል አሳስበዋል፡፡

"ስልጣንና ኃላፊነት ሁሉ ከፈጣሪ ነው፣  በጉልበት፣ በዘረኝነት፣ በቡድን፣ ወይም በአድማ ስልጣንን ለማግኘት ሲል በሥላሴ አምሣል የተፈጠረን ሰው ደም ማፍሰስ ግን የተረገመ እንዲሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ይናገራል" ብለዋል፡፡

ሰዎች ፍትህ ሲዛባባቸው፣ አቅም የሌላቸው ሲቸገሩ፣ ከቀያቸው ሲሰደዱ በእነርሱ ምትክ ካህናት ያለምንም ልዩነት ስለእነርሱ መናገር እንደሚጠባቅባቸውም አመልክተዋል፡፡

ግጭት በዘላቂነት እንዲወገድ ጉቦን ከመቀበል ይልቅ በመቃወም እና ዘረኝነትን በማውገዝ በምትኩ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በመስበክ ተግተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ቄስ መልዓከ-ሠላም ገብረማርያም በሰጡት አስተያየት "አሁን በየአካባቢው ለተከሰተው ግጭት እኛ የኃይማኖት አባቶች በዘር በመከፋፈል አስተዋጽኦ አድርገናል "ብለዋል፡፡

የተሰጣቸውን ኃላፊነትት በሚገባ አለመወጣታቸው እንጂ ቤተክርስቲያኗ  ዘረኝትን በመዋጋት ሠላምን እና ፍቅርን የሚሰብክ ቀኖና ያላት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው ለካህናት ማንቂያ ደወል እንደሆነ ጠቅሰው በቀጣይ ከሃገረ ስብከት እስከ ንስሃ አባት ካለው መዋቅር ጋር በመተባበር እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተሰጠው ስልጠና ከ300 የሚበልጡ በአሶሳ ሃገረ ስብከት ስር የሚገኙ ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና ምዕመናን ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም