የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር መግባባት ላይ መድረሱን አስታወቀ

64

አዲስ አበባ ታህሳስ 23/2011 የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት  ሚኒስቴር ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ጋር መግባባት ላይ መደረሱን አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአሁኑ ወቅት ያሉበት ደረጃና ቀጣይ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለመመለስ ዘለግ ያለ ጊዜና ጥረት ጠይቋል። 

በተማሪዎች ግንባር ቀደም ተሳትፎ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ በታዋቂ ግለሰቦች፣ የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች፣ በዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባላትና  የአስተዳደር አካላት እንዲሁም በሌሎች አካላት ጥረት በዩኒቨርሲቲው የነበረውን የሰላምና መረጋጋት እጦት ለመፍታት ተችሏል ብለዋል።

ዶክተር ሂሩት እንደተናገሩት በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የስጋት ምንጮች ላይ የመወያየት እና የተማሪዎችን ስነ ልቦና የማረጋጋት ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።

በተከናወኑት ውይይቶችም ተማሪዎች በአሁኑ ወቅት ወደ ክፍል ለመግባት ሆነ በግቢው ውስጥ ለመኖር ስጋት እንዳለባቸውና በዩኒቨርሲቲው የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉት ችግሮች እንዲፈቱላቸው መጠየቃቸውን አንስተዋል።

እንደ ዶክተር ሂሩት ገለጻ በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ያሉት የፀጥታ ችግሮችና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ከተፈቱ በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን ለመቀጠል ከተማሪዎቹ ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል።

ሆኖም አንዳንድ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ረዘም ላለ ግዜ የስነ ልቦና ጫና ባለው ሁኔታ ውስጥ በመቆየታቸው የዕረፍት ጊዜ እንዲሰጣቸው በመጠየቃቸው እሰከ ጥር 1 ቀን 2011ዓ.ም ድረስ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዳይቀጥል መወሰኑን ነው ዶክተር ሂሩት የገለጹት።

ይህም በዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ፣ በሚኒስቴሩና በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በአስቸኳይ መሰራት ያለባቸውን ስራዎች ለማከናወንና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን አላማ መድረጉን ነው ያስረዱት ፡፡

ዶክተር ሂሩት እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው መቆየት ለሚፈልጉ ተማሪዎች ትምህርት ባይኖርም አገልግሎት እየተሰጣቸው ይቆያሉ።

በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲም ሆነ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች የብሄር ግጭቶች ሳይሆኑ በአገሪቱ ያለውን ለውጥ የሚቃወሙ ኃይሎች ነጸብራቅ መሆኑንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ውጭ በሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱ አልተቋረጠም ብለዋል።

"በተማሪዎቻችን መካከል የብሄር ግጭት የለም" ያሉት ሚኒስትሯ፤ የብሄር መልክ የሚያስመስል ያልተገባ እንቅስቃሴ ግን እየተስተዋለ መሆኑን ተናግረዋል።

በጥቂት ግለሰቦች መካከል የተፈጠረ ግጭት ወደ ቡድን ቀጥሎም ወደ ብሄር መሰል ግጭት እንዲያመራ እየተደረገ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በሌሎች ወጣቶች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች ባለፉት አመታት በወጣቶች ሰብዕና ላይ የተዘባ አመለካከት በመፈጠሩና የሰብዕና ግንባታ ላይ ባለመስራታችን የተነሳ ችግር ነው ያሉት።

በመሆኑም የሰብዕና ግንባታ ላይ ያተኮሩ ትምህርቶች፣ ስራ ፈጣራንና የአገርን ችግር ለመፍታት የሚያስብ ዜጋን ለመፍጠር የሚያስችል የትምህርት ፖሊሲ የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኢትዮጵያዊነት የሚጎለብትበት ማዕከላት እንዲሆኑም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን የከፍተኛ ትምህርት ማህበረሰቡ የሰላም ባለቤት እንዲሆን ከኃይማኖትና ከድርጅት እንቅስቃሴ ነጻ እንዲሆኑ ጠንካራ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተማሪዎች ቅሬታ መነሻ የሆኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ላይም በፍጥነት እየተሰራ መሆኑን እና ሌሎች የስጋት ምንጮች ተለይተው እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም