ሆስፒታሉ የጥገና ማዕከልና የህክምና መስጫ ቁሳቁሶች ድጋፍ አገኘ

85

መቀሌ ታህሳስ23/2011 የመቀሌ ዓይደር ስፔሻላይዝ ሪፈራል ሆስፒታል ከ2 ሚሊዮን 300ሺህ ብር በላይ  ግምት ያላቸው የጥገና ማዕከልና የህክምና መስጫ ቁሳቁሶች ድጋፍ አገኘ፡፡

ድጋፉ የተገኘው ከኮርያ አለም አቀፍ የጤና ጥበቃ ፋውንዴሽን ሲሆን  ይሄው ድርጅት ከትግራይ ክልል የተለያዩ ሆስፒታሎች ተወጣጥተው በሆስፒታሉ  ለሁለት ሳምንታት ያሰለጠናቸውን የህክምና መሳሪያ ጥገና ባለሙያዎችን አስመርቋል።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ርዕየ ኢሳያስ ለኢዜአ እንዳሉት  ፋውንዴሽኑ ለሆስፒታሉ ከሰጠው ድጋፍ ውስጥ የህክምና መሳሪያዎች ጥገናና ስልጠና አገልግሎት የሚውል አንድ ማዕከል ይገኝበታል፡፡

ማዕከሉ  ከአንድ ሚሊዮን 300ሺህ ብር  በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ  ሲሆን በተጨማሪም  1 ሚሊዮን ብር  ግምት ያላቸው የተለያዩ የህክምና መስጫ ቁሳቁሶችን ለሆስፒታሉ ለግሷል።

ዘመናዊ የደም ግፊት መለኪያ ፣የልብ ምት መቆጣጠሪያ፣የቆዶ ጥገና ህክምና መሳሪያና የኤሌክትሪክ ንዝረት መቆጣጠሪያ ፋውንዴሽኑ በድጋፍ ከሰጣቸው ቁሳቁሶች መካከል እንደሚገኙበት  ሜዲካል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ድጋፉ  ብቃት ያላቸውን የህክምና ባለሙያዎች በማሰልጠን ለህክምና የሚወጣውን ወጭ 50 በመቶ መቀነስ እንደሚያስችል ዶክተር ርዕየ አስታውቀዋል፡፡

በፋውንዴሽኑ  የኢትዮጵያ አስተባባሪ ሚስተር ዳኒ ኪም  ፋውንዴሽኑ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በህክምናው ዘርፍ የተሟላ  የህክምና መሳሪያዎች ጥገና  እንዲኖር በተግባር የተደገፈ የሰው ኃይል ስልጠና ለመስጠት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ከሰልጣኞች መካከል  አቶ ጉዑሽ ኪዱ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በተግባር ካላይዋቸው የህክምና መሳሪያዎች ጋር እንዳስተዋወቃቸው ገልጸዋል።

የህክምና መሳሪያዎች ጥራት መፈተሻ ማሽኖችን ጨምሮ በጠቅላላ ህክምና መሳሪያዎች ላይ የሚያጋጥሙ ዋና ዋና ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና በመውሰዳቸው ለሙያቸው ተጨማሪ አቅም እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል። 

ሌላዋ ሰልጣኝ ወጣት ታሪክ ንጉሴ በበኩሏ ስልጠናው በሆስፒታሎች  በእውቀት ማነስ ተበላሽተው እየተጣሉ ያሉ የህክምና መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግራለች ።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የባዮ ሜዲካል ኢንጅነሪንግ  ባለሙያ አቶ አስፋው አፈወርቂ  ፋውንዴሽኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየሰጣቸው ያሉ አጫጭር ስልጠናዎች፣ የህክምና መሳሪያ ጥገና እና የስልጠና ማዕከላት ግንባታ ለህክምናው ዘርፍ መጠናከር አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ፋውንዴሽኑ  የመቀሌ ዓይደር ሆስፒታል  የህክምና መሳሪያ ጥገናና ስልጠና ማዕከል በሀዋሳ፣ ጎንደርና ጅማን ጨምሮ በሀገሪቱ ከተገነቡት ሰባት ተመሳሳይ ማዕከላት  ውስጥ አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም