ከጀግኖች አባት አርበኞች የተረከብናትን አገር አንድ ሆነን ልናቆይ ይገባል…. የጉዞ አድዋ ተጓዥ ወጣቶች

565

ሀረር ታህሳስ 23/2011 ጀግኖች አባት አርበኞች አንድ ሆነው ለትውልድ ያስተላለፉትን አገር አንድነትን በማጠናከር ልናቆይ ይገባል ሲሉ የጉዞ አድዋ ተጓዥ ወጣቶች ተናገሩ።

” ፍቅር ለኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!” በሚል መሪ ቃል መነሻውን ሐረር ከተማ መድረሻውን ደግሞ በታሪካዊቷ አድዋ ያደረገው ጉዞ አድዋ የወጣቶች የሰላም ጉዞ ትናንት ተጀምሯል።

የጉዞው አስተባባሪ ወጣት መሀመድ ካሳ በልዑል ራስ መኮንን መሪነት ተነስቶ አድዋ የደረሰው ቀዳሚው ጦር ከምስራቁ የአገሪቱ ክፍል በመሆኑ ይህን ለማስታወስ ሲባል ዘንድሮ የእግር ጉዞው ከሐረር ከተማ መጀመሩን ተናግሯል።

በወቅቱ አባት አርበኞች በግዛትና በተለያዩ ጉዳዮች የአመለካከት ልዩነት ቢኖራቸውም በአገር ጉዳይ ላይ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በነበራቸው አንድነት የውጭ ወራሪን መመከት እንደቻሉ አስታውሷል።

“በአሁኑ ወቅትም ሕብረተሰቡ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ቢኖረውም የእርስ በርስ አንድነቱን በማጠናከር ሀገሩን ጠብቆ ማቆየት ይኖርበታል” ሲል ወጣት መሀመድ ተናግሯል።

በእግር ጉዞው ከሐረር፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተማ የተወጣጡ 40 የሚጠጉ ወጣቶች እንደሚካፈሉ የገለጸው ሌላው አስተባባሪ ወጣት ያሬድ ሹመቴ፣ ጉዞው 1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍንና ለሁለት ወራት እንደሚቆይ ተናግሯል።

“ከአድዋ ታሪክ የምንማረው አንድነትን፣ ሕብረት፣ ፍቅር፣ ሰላምንና መደማመጥን በመሆኑ ይህንንም መተግበር ከቻልን ለአፍሪካ ምሳሌ የምትሆን አገር ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንችላለን” ብሏል።

የዘንድሮ የሰላም ጉዞ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስፈላጊ መሆኑን የጠቆመው ወጣት ያሬድ በጉዞው መስመር ላይ በሚገኙ ከተሞችና መንደሮች  ተጓዞቹ ስለ አገር ሰላምና አንድነት ትምህርት እንደሚሰጡ ገልጿል።

በጉዞው ሲሳተፍ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ የገለጸውና ከድሬዳዋ የመጣው ወጣት ወንደሰን ኪዳኔ በበኩሉ “በጉዞ ወቅት ከልዩነት ይልቅ አንድነትን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ለወጣቱ ትምህርት እየሰጠሁ እጓዛለው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

አባት አርበኞች በአንድነት ተጋድለው ያስረከቡንን አገር ዛሬ ያለነው ትውልድ የእርስ በርስ አንድነትን በማጠናከር ጠብቀን ልናቆይ ይገባል ሲል ተናግሯል።

በ2006 ዓ.ም ከአዲስ አበባ – አድዋ በአምስት ሰዎች የተጀመረው የእግር ጎዞ ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን የ” ጉዞ አድዋ የሰላም ተጓዦችም ” ጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።