በባህር ዳር ከተማ በአንድ የፖሊስ አባል መኖሪያ ቤት 498 ህገ ወጥ ሽጉጦች ተያዙ

163

ባህር ዳር ታህሳስ 23/2011 በባህር ዳር ከተማ በአንድ የፖሊስ አባል መኖሪያ ቤት 498 ቱርክ ሰራሽ ህገ ወጥ ሽጉጦች ተደብቀው መያዛቸውን የከተማው ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የወንጀል ምርመራ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር አየልኝ ታክሎ ለኢዜአ እንደገለጹት ህገ ወጥ መሳሪያው ትናንት ከምሽቱ 1፡30 ላይ በቁጥጥር ስር የዋለው ህዳር 11 ክፍለ ከተማ በሚገኘው የግለሰቡ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው።

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያው በፖሊስ ሊያዝ የቻለው ከህብረተሰቡ ለፖሊስ የደረሰውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ በተካሄደ ጥንቃቄ የተሞላበት ፍተሻ መሆኑን ተናግረዋል።

"በከፍተኛ የአመራር ደረጃ የሚገኘው የፖሊስ አባሉ የህዝብና የሀገር ኃላፊነትን ወደ ጎን በመተው በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ተጠርጥሮ መያዙ ጉዳዩን አሳዛኝ ያደርገዋል" ብለዋል።

ተጠርጣሪው ግለሰብ በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ኮማንደር አየልኝ፣ በቀጣይም ከጉዳዩ ጋር ግንኙት ያላቸው ተጨማሪ አካላትን ለመያዝ የማጣራት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ያለውን አለመረጋጋት ተከትሎ በከተማው ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንደሚስተዋል ጠቁመው፣ በተለያየ ጊዜ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻም የተለያዩ መሳሪያዎች መያዛቸውን አስታውሰዋል።

"በፖሊስ በኩል የማጣራቱና የምርመራ ሥራው እንደተጠናቀቀም መረጃው ለህዝብ ይፋ ይሆናል" ብለዋል።

ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካሉ ጎን ሆኖ እየሰጠ ያለውን ጥቆማ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጠቆሙት ምክትል ኮማንደር አየልኝ፣ ማንኛውም አጠራጣሪ ጉዳይ ሲገጥመው ለሚመለከተው የፀጥታ አካል ፈጥኖ እንዲያሳውቅ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም