የብድርና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ ባለማግኘታችን ወደ ሥራ መግባት አልቻልንም ፡- የአጋርፋ ወረዳ ወጣቶች

791

ጎባ ታህሳስ 23/2011 ተደራጅተን አስፈላጊውን መስፈርት ብናሟላም የብድርና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ ባለማግኘታችን ወደ ሥራ መግባት አልቻልንም ሲሉ በባሌ ዞን የአጋርፋ ወረዳ ወጣቶች ቅሬታቸውን ገለፁ።

የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም በበኩሉ ከዚህ በፊት የሰጠው ተዘዋዋሪ ብድር በወቅቱ ባለመመለሱ አዲስ ብድር መስጠት እንዳልቻለ ገልጿል፡፡

የአጋርፋ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ብርሃኑ አበበ ከአንድ ዓመት በፊት ከሌሎች አምስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተው በማህበር ቢደራጁም የብድር አገልግሎት ባለመግኘታቸው ወደ ስራ መግባት እንዳልቻሉ ተናግሯል፡፡

”ችግሩን በማስመልከት ከወረዳ እስከ ዞን ላሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ብናሳውቅም እስከ አሁን መፍትሄ ባለመግኘታችን ከቤተሰብ ጥገኝነት መላቀቅ አልቻልንም” ብሏል፡፡

ሌላው የዚሁ ወረዳ ኗሪ ወጣት አስቻለው መንግስቱ  በበኩሉ  ከአንድ ዓመት በፊት ከአራት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ተደራጅተው በእንስሳት ማድለብና በወተት ላሞች እርባታ ሥራ ለመሰማራት የሚያስፈልጋቸውን መስፈርት አሟልተው ጉዳዩ ለሚመለከተው ፅህፈት ቤት ጥያቄ አቅርበው ነበር ።

“በመስፈርቱ መሰረት የሥራ ዕቅድ አዘጋጅተን ብድሩን ለማግኘት በቅድመ ሁኔታነት የሚጠበቅብንን 10 በመቶ ቆጥበናል” ያለው ወጣት አስቻለሁ የገንዘብ ብድሩንም ሆነ ለእርባታ የሚሆነውን ቦታ ባለማግኘታቸው ወደ ሥራ ሳይገቡ መቅረታቸውን ገልጿል።

“ከብድር እጦትና ከመስሪያ ቦታ ችግር የተነሳ ከቤተሰብ ጥገኝነት አልተላቀቅንም ” ያሉት ወጣቶቹ፣ የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ጠይቀዋል።

የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም የባሌ ዞን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደፎ ኡመሮ በሰጡት ምላሽ ከብድር አቅርቦት ጋር ተያይዞ ወጣቶቹ የሚያነሱት ቅሬታ ትክክል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ችግሩ የተከሰተው ተቋሙ ባለፉት ዓመታት ለደንበኞቹ ያበደረው ተዘዋዋሪ  ፈንድ በወቅቱ ባለመመለሱ የማበደር አቅሙ እየቀነሰ በመምጣቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሃላፊው እንዳሉት ባለፉት ዓመታት ከአንድ ሺህ በሚበልጡ ማህበራት ስር ለተደራጁ ወጣቶች ተቋሙ አበድሮ በዚህ ወቅት መመለስ ከነበረበት 87 ሚሊዮን ብር ውስጥ እስከ አሁን 54 በመቶ ብቻ መመለሱን በማሳየነት አቅርበዋል፡፡

ተዘዋዋሪ ብድሩ በወቅቱ አለመመለሱ የተቋሙን የማበደር አቅም ከመፈታተኑም በሻገር ለሌሎች የመነሻ ካፒታል የሚፈልጉ ወጣቶች  ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያስከተለ በመሆኑ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሰሩበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ሀላፊው እንዳሉት ተቋሙ በተያዘው በጀት ዓመት ለማበደር በእቅድ ከያዘው 70 ሚሊዮን ብር መካከል እስከ አሁን 9 ሚሊዮን ብር ብቻ ማበደር መቻሉ በዘርፉ ብዙ መስራት እንደሚጠብቅ አመላካች ነው ፡፡

የዞኑ የስራ እድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጫልችሳ ዘውዴ በበኩላቸው መንግስት ለወጣቶች ያመቻቸው ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመፈተሽ ችግሩን ለመፍታት እየተሰረ ነው፡፡

የመስሪያ፣ የመሸጫ ቦታዎችና ሼዶች እጥረት ለመቅረፍ በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ከ117 የሚበልጡ ሼዶችን እያስገነቡ ሲሆን ያለአግባብ በማይገባቸው ሰዎች ከዚህ በፊት የተያዙትንም በማስለቀቅ ለወጣቶቹ እንዲተላለፉ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነው፡፡

” ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ውይይትና ስምምነትም ባለፈው የበጀት ዓመት ተደራጅተው ወደ ሥራ ያልገቡ ወጣቶች ዘንድሮ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ በአካባቢው ላይ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ሌሎች የመንግስት ተቋማት ጋር በቅንጂት እየተሰራ ነው ” ብለዋል።

”በበጀት ዓመቱ ከ49 ሺህ የሚበልጡ አዳዲስ ስራፈላጊ ወጣቶችን በተለያዩ የስራ ዘርፍ እንዲሰማሩ እየተሰራ ነው” ያሉት አቶ ጫልችሳ ባለፉት ወራትም ከ20ሺህ የሚበልጡትን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

ሀላፊው እንዳሉት በተለይ ከብድር አመላለስ ጋር ተያይዞ እየተፈጠረ የሚገኘውን ክፍተት ለመሙላት ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በሁሉም የሴክተርና በየደረጃው በሚገኙ አመራሮች በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በባሌ ዞን ከ2009 ዓ ም ጀምሮ መንግስት ባመቻቸው ብድር ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ለተደራጁ ወጣቶች መሰራጨቱን የስራ እድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡