ለውጭ ገበያ ከቀረበ አኩሪ አተር 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

459

አዳማ ታህሳስ 23/2011 በበጀት ዓመቱ አራት ወራት ለውጭ ገበያ ከተላከ የአኩሪ አተር ምርት ሽያጭ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን አሰታወቀ።

በወራቶቹ 5 ሺህ 24 ቶን የአኩሪ አተር ምርት ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት ተልኮ ለገበያ መቅረቡን ባለስልጣኑ ገልጿል ።

በባለስልጣኑ የስልጠናና አቅም ግንባታ ቡድን መሪ አቶ ሰለሞን ማስረሻ ለኢዜአ እንደገለፁት ምርቱ በዋናነት የተላከው ለህንድ፣ ቻይና፣ ሲንጋፖርና ቬትናም ገበያዎች ነው።

እንደ ቡድን መሪው ገለጻ ምርቱ ለውጭ ገበያ የተላከው በግል አቅራቢ ነጋዴዎች አማካኝነት ነው።

ከታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የሽምብራና የአኩሪ አተር ምርት ወደ ዘመናዊ የግብይት ሰንሰለት እንዲገባ መደረጉንም ተናግረዋል ።

“በሀገሪቱ በአመት ከ800 ሺህ ኩንታል በላይ አኩሪ አተር ይመረታል” ያሉት ቡድን መሪው ምርቱ ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዲገባ መደረጉ አምራቹንና ተቀባዩን በቀጥታ በማገናኘት አርሶ አደሩ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ የሚያስችለው መሆኑን ገልፀዋል ።

የአኩሪ አተር ምርት በአዲስ አበባ፣ አሶሳ፣ ፓዌ፣ ቡሬ፣ ነቀምትና ጎንደር የሽምብራ ምርት ደግሞ በአዳማ፣ አዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ ኮምቦልቻና ቡሬ  የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቅርንጫፎች ላይ ግብይት እየተከናወነ መሆኑን ቡድን መሪው አስታውቀዋል ።