ለላሊበላ የገናን ክብረ በዓል የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ ነው

73

ወልድያ ታህሳስ 23/2011 ዓመታዊው ላሊበላ የገናን ክብረ በዓል ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት አስታወቀ። 

በበዓሉ ለመታደም ከ200ሺ በላይ እንግዶች ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊና የመስተንግዶ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ስጠው ኃይሉ እንደገለጹት ታህሳስ 29/ 2011 ዓ.ም. የሚውለው  የገና በዓል በሰላምና በድምቀት ለማክበር ከመንግስት ፣ ከካህናትና ከማህበረሰቡ የተውጣጡ አካላት በአባልነት ያቀፉ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፡፡

የተቋቋሙትም የሰላምና የጸጥታ፣ የመስተንግዶ፣ የጽዳት፣ የገቢ ማሰባሰብና የመሰረተ ልማት ኮሚቴዎች ሲሆኑ ድርሻቸው ተከፋፍለው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡

ሰላምን ለማስከበር ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር በመተባበርና የፍተሻ ኬላዎችን በማቋቋም ገቢና ወጪውን የመከታተል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው የእንግዶችን ጸጥታና ንብረት የሚጠብቁ በገጠርና ከተማ  የጸጥታ አካላት መመደባቸውን አስረድተዋል፡፡

ቤትና አልጋ መከራየት ለማይችለው እንግዶች  የሚያርፍባቸው አራት ሰፋፊ ቦታዎች ተደልድለው እንደተዘጋጁ ጠቁመው  በየአካባቢውም ጊዜያዊ መጸዳጃ ቤቶችና የውሀ ማከፋፈያዎች መሰናዳታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ላሊበላ ሆስፒታልን ጨምሮ በጤና ተቋማት ድንኳኖች ተተክለው 24 ሰዓት ለእንግዶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን መመደባቸውን አመልክተዋል፡፡

የቀይ መስቀል ወጣቶችም የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ለመስጠትና የተጠፋፉ ቤተሰቦችን ለማገናኘት ተዘጋጅተዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሚመጡ ቱሪስቶችን የሚያስተናግዱና የተለያዩ የውጭ ቋንቋዎችን የሚናገሩ 130 ያህል አስጎብኝ  አስተርጓሚዎች ተዘጋጅተው እየተጠባበቁ ነው፡፡

የዘንድሮውን ገና በዓል ለየት የሚያደርገው በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ እንደ ኤርትራ ካሉ ጎረቤት ሀገራት ሳይቀር እንግዶች በነፃነት እየመጡ መሆኑም ተመልክቷል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም