በአማራ ክልል ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚሞተው ሰው ቁጥር እየጨመረ ነው፡- የክልሉ ጤና ቢሮ

885

ባህርዳር ታህሳስ 23/2011 በአማራ ክልል ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚሞተው ሰው ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ጤና ቢሮ የፈውስ ህክምና ክፍል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ንዑስ የስራ ሂደት አስተባባሪ ዶክተር ሞላ ገደፋው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በተያዘው አመት በተካሄደ ጥናት በክልሉ ከሚሞቱ 10 ሰዎች መካከል ከአምስት እስከ ስድስት የሚሆኑት የሚሞቱት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች መሆኑ ተረጋግጧል።

በአገር አቀፍ ደረጃ በገዳይነታቸው የሚታወቁት  የደም ግፊት፣ ከደም ግፊት ጋር ተያይዞ የሚከሰት ስትሮክ፣ስኳር፣ ካንሰርና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የክልሉን ህዝብ ለጉዳት እየዳረጉት ይገኛሉ።

የደም ግፊትና የስኳር በሽታዎች ለኩላሊትና ሌሎች ተያያዥ በሽታዎች መንስኤ በመሆናቸው  ህብረተሰቡ እነዚህን በሽታዎች አስቀድሞ በመመርመር መከላከልና መቆጣጠር ሲገባው በችልተኝነት ለአደጋ እየተጋለጠ መሆኑን አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡  

ዶክተር ሞላ እንዳሉት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከአልኮል መጠጥ ብዛት፣ ቅባት የበዛባቸውንና ጣፋጭ ምግቦችን ከማዘውተር፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ካለማድረግ፣ ለተለያዩ ሱሶች ተገዥ በመሆን ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው።

በተለይ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ የመከሰት እድላቸው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በአማራ ክልል ከ200 በላይ ጤና ጣቢያዎች ላይ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች የደም ግፊትና የስኳር በሽታዎችን ቅድመ ምርመራ ለማድረግ ስልጠና ቢሰጣቸውም ህብረተሰቡ ቀድሞ በመመርመር እራሱን የመከላከልና የመቆጣጠር ልምዱ ያልዳበረ በመሆኑ የሚፈለገው ውጤት አለመምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ተመርምረው ራሳቸውን ያወቁትም በህክምና ባለሙያዎች የሚነገራቸውን ምክረ ሀሳብ ተቀበልው ክትትል ስለማያደርጉ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ዶክተር ሞላ ተናግረዋል፡፡

አብዛኛው ሰዎች ቅድመ ምርመራ ሳያደርጉ ችግሩ ከተባባሰ በኋላ ስለሚመጡ ታክመው የመዳን እድላቸው የመነመነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ ኃኪም ዶክተር ሳሙኤል ሁነኛው ናቸው።

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንና ከነሱ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ በሽታዎችን አክሞ ማዳን የማይቻልበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት ህብረተሰቡ ቀድሞ በመመርመር ራሱን ከበሽታው መከላከልና መቆጣጠር እንዳለበት ዶክተር ሳሙኤል አሳስበዋል፡፡

የስኳርና የደም ግፊት በሽታ እንዳለባቸውና ክትትል እንዲያደርጉ ቢነገራቸውም የኃኪሞችን ምክረ ሀሳብ ተቀብለው ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ኩላሊታቸው እየተዳከመ መምጣቱን የገለጹት ደገሞ ወይዘሮ እናና ስንታየሁ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በፈለገ-ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት ህክምና እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

“ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በወቅቱ ካልታከሙ በሚያስከትሉት ጉዳት ላይ ግንዛቤ ስለሌለኝ አስከፊ ለሆነው የኩላሊት ህመም ልዳረግ ችያለሁ” ያሉት ወይዘሮ እናና ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በፈለገ-ህይወት ሆስፒታል ወላጅ አባቱን በማስታመም ላይ ያለው ወጣት ደጋረገ ጌቴ በበኩሉ አባቱ የደም ግፊት በሽታ እንደተከሰተባቸው ምርመራ ቢያደርጉም በወቅቱ ክትትል አለመጀመራቸው ለከፋ ችግር እንደዳረጋቸው አስረድቷል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የተደረገ ጥናት እንደሚያያሳየው 15 ዓመትና ከዚያ በላይ የዕድሜ ክልል ካሉ የህብረተሰብ ክፍሎች 16 ከመቶ የሚሆኑት የደም ግፊት ተጠቂዎች ናቸው። 5 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በስኳር ህመም እንደሚያዙ ተመላክቷል፡፡