መንግስት ወጣቱን በማሳተፍ የጀመራቸውን የለውጥ ስራዎች በማጠናከር የማይፈታ ችግር እንደማይኖር ገለፀ

63
አዲስ አበባ ግንቦት 17/2010 መንግስት ወጣቱን በማሳተፍና የጀመራቸውን የለውጥ ስራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል ችግሮችን እንደሚፈታ ጽኑ እምነት እንዳለው ገለፀ። የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ ህዝቡንና የለውጥ ሞተር የሆነውን ወጣቱን ኃይል በመያዝ የማይፈታ ችግር እንደማይኖር ጽኑ እምነት እንዳለው አስታውቋል። መንግስት የህዝብን ጥያቄ ለመመለስና አገሪቷ ሰላሟ የተረጋገጠ፤ ዕድገቷም የሰመረ፤ ማህበረ ባህላዊ አውዷም ያማረ ይሆን ዘንድ በከፍተኛ ትጋት እና ፍጥነት በመረባረብ ላይ እንደሚገኝ በመግለጫው ተመላክቷል። በመንግስት በኩል የሚደረጉ ጥረቶችና እየተኼደባቸው ያሉ አቅጣጫዎች አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ ያሉ ቢሆንም ከችግሮቻችን ስፋት እና ካልተመለሱ ጥያቄዎች ብዛት አንጻር አሁንም ብዙ የቤት ስራዎች እነደሚቀሩም አጽንኦት ሰቶታል። መንግስትም ይህንኑ በመረዳት በተሰሩ ስራዎች ሳይኩራራ ከሠራቸው ስራዎች ይልቅ ባልሠራባቸው ሥራዎች በፍጹም ቁርጠኝነት እና ተነሳሽነት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል። በመሆኑም መንግስት ወጣቱን በማሳተፍ የጀመራቸውን የለውጥ ስራዎች በማጠናከር እስከታችኛው መዋቅር ድረስ እንዲወርዱ ለማድረግ የሚጠበቅበትን ሁሉ ሚና እንደሚወጣና በዚህም የማይፈታ ችግር  እንደማይኖር ገልጿል። የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ተቀምጧል።   በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ ግንቦት 17 ቀን 2010 ዓ.ም ህዝባችንን እና የለውጥ ሞተር የሆነውን ወጣት ኃይላችንን ይዘን የማንፈታው ችግር አይኖርም መንግስት የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ እና ሀገራችንም ሰላሟ የተረጋገጠ፤ ዕድገቷም የሰመረ፤ ማህበረ ባህላዊ አወዷም ያማረ ይሆን ዘንድ በከፍተኛ ትጋት እና ፍጥነት በመረባረብ ላይ ይገኛል፡፡ በመንግስት በኩል የሚደረጉ ጥረቶች እና እየተኬደባቸው ያሉ አቅጣጫዎች አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ ያሉ ቢሆንም ከችግሮቻችን ስፋት እና ካልተመለሱ ጥያቄዎች ብዛት አንጻር ግን አሁንም ብዙ የቤት ስራዎች ከፊታችን ይጠብቁናል፡፡ መንግስትም ይህንኑ ስለሚረዳ በተሰሩ ስራዎች ባለመኩራራት  ከሰራናቸው ስራዎች ይልቅ ያልሰራናቸው ይበዛሉ በሚል ስሜት በፍጹም ቁርጠኝነት እና ተነሳሽነት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ባለፉት ሁለት ወራት በሀገራችን የታየው አንጻራዊ ሰላም፣ መረጋጋት እና ሀገራዊ አንድነት አሁን ባለበት ደረጃ ላይ ይገኝ ዘንድ አስተዋጽኦ ያደረጉ ወዳጆቻችን፣ አጋሮቻችን እና ሌሎችም አካላት ብዙ ቢሆኑም ዋናው ተዋናይ እና የጉዳዩም ባለቤት ግን ሆደሰፊው እና አስተዋዩ ህዝባችን ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት ይህ ታላቅ ህዝብ ክብር፣ ሰላም፣ ፍትህ፣ እና ዴሞክራሲ፣ ፈላጊ ዜጋ በመሆኑ ብቻ ላቅ ያለ አገልግሎት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ያስፈልገዋል ብሎ ያምናል፤ ይገባዋልም፡፡ በሀገራችን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ከተደረገ ወዲህ ለህዝብ ጥያቄዎች እና በተጨባጭም በሀገራችን ውስጥ ላሉ መፍትሄ የሚሹ ጥያቄዎች ሁነኛ ምላሽ ለማበጀት የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት ጥረት ተደርጓል፡፡ በሀገር ውስጥ ያሉ እና በተለያዩ ሰበቦች በየእስር ቤት ለሚገኙ ወገኖች የይቅርታ እና የሰላም በሮችን በመክፈት የሀገራችንን ሁለንተናዊ ድባብ በሰላማዊ መንፈስ ለመቃኘት ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከጎረቤት ሀገራት ጋር እና ወደ መካከለኛው ምስራቅም በመጓዝ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባደረጉት የስራ ጉብኝት በርካታ ዲፕሎማስያዊ ድሎችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን እና የልኡካን ቡድናቸው በተገኙባቸው ሀገራት ሁሉ ቅድሚያ ሰጥተው ያነሱት የነበረው አጀንዳ የዜጎቻችን ደህንነት እና ክብር ጉዳይ በመሆኑ በተጎበኙት ሀገራት ሁሉ የነበረው አቀባበል እና መረዳት የመንግስታችንን የዲፕሎማሲ ተግባቦት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ነበር ብሎ መግለጽ ይቻላል፡፡ መንግስት በእነዚህ ዲፕሎማስያዊ ድሎች እና በሀገር ውስጥም በውጭም በተመዘገቡ ስኬቶች ሳይዘናጋ የጀመረውን የሰላም፣ የፍትህ፣ የአንድነት እና የልማት እንቅስቃሴ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከጎረቤት  እና ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር በልማት፣ በኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እና በህዝብ ለህዝብ ውድጅቶች አብሮ በመስራት አብሮ ለመጠቀም የተደረሰባቸው ስምምነቶች እውን ይሆኑ ዘንድ በትጋት ይሰራል፡፡ በውጭ ለሚመዘገቡ ድሎች ጽኑው መሰረት ያለው በሀገር ውስጥ እንደሆነ መንግስት በውል ይገነዘባል፡፡ በመሆኑም በሀገር ወስጥ የጀመራቸውን ዙርያ መለስ የለውጥ ስራዎች እጅጉን በማጠናከር እስከታችኛው መዋቅር ድረስ እንዲወርዱ የሚጠበቅበትን ሁሉ ያደርጋል፡፡ ችግሮቻችን ብዙ፣ መሰረታቸውም ጥልቅ በመሆኑ በምንፈልገው ስፋት እና ጥራት ያለመሄድ እክል ቢኖርም ህዝባችንን እና የለውጥ ሞተር የሆነውን ወጣት ሀይላችንን ይዘን የማንፈታው ችግር እንደማይኖር መንግሥት ለማረጋገጥ ይወዳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም