ህጉ የሚጠበቀውን ውጤት እንዳላመጣ ተገለጸ

848

መቀሌ ታህሳስ 22/2011 ትምባሆን ለመቆጣጠር ስራ ላይ የዋለው ህግ የሚጠበቀው ውጤት አለማምጣቱን  የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በጉዳዩ ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ ትናንት በዓዲግራት ከተማ   ተካሂዷል፡፡

በባለስልጣኑ  የህግ ማእቀፍና የህክምና ዳይሬክተር ወይዘሮ አብርሄት ግደይ በመድረኩ እንዳሉት ትምባሆን ለመቆጣጠር ስራ ላይ የዋለው ህግ የተፈለገውን ለውጥ ያላመጣው አስገዳጅ ባለመሆኑና ህብረተሰቡ በንቃት የሚሳተፍበትን አሰራር ባለማካተቱ ነው፡፡

ትምባሆን ለመቆጣጠር በ2006 ዓ.ም  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  ጸድቆ ስራ ላይ እንዲውል የተደረገው ህግ የአስገዳጅነትና የቅጣት አንቀጾችን አካቶ እንዳልያዘ አመልክተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በሀገር አቀፍ ደረጃ  በየዓመቱ  በርካታ ሰዎች  የትምባሆ ምርትን በመጠቀም  ለህልፈት እንደሚዳረጉ አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም ህጉን በህዝብ ንቅናቄ ለማስፈጸም የሚያስችል የአሰራር፣የማስፈጸም አቅምና የግብዓት አለመሟላት ችግሮች  ለውጡ የሚፈለገውን ያህል እንዳይሆን አድርጎታል።

የትምባሆ ምርትን በተለይ ሲጋራ ማጨስን ህዝብ በሚበዛባቸው ስፍራዎች እንዳይሆን የሚከለክለውን ህግ በሀገሪቱ ስራ ላይ እንዲውል ከተደረገ በኋላ  ለውጥ ያመጣው የትግራይ ክልል ብቻ መሆኑን ዳይሬክተሯ  ተናግረዋል።

ክልሉ ትምባሆን የሚጸየፍ ማህበረሰብ በመፍጠርና የራሱን ደንብ በማውጣት ጠንካራ ስራ በማከናወኑ ለውጥ ማምጣቱናና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሽልማት መብቃቱን አስታውሰዋል።

ህጉ በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ለውጥ እንዲያመጣ ለማስቻል የቅጣትና የአስገዳጅነት ጉልበት እንዲኖረው እንደገና የማሻሻያ ስራ እንደተደረገበት  ዳይሬክተሯ አመልክተዋል፡፡

የተሻሻለው መመሪያ በቀጣይ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚጸድቅና ስራ ላይ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡

የትምባሆ ምርትን የሚጸየፍ ማህበረሰብ ማፍራት ዋንኛዎቹ የመፍትሄ እርምጃዎች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በውይይት መድረኩ የተገኙት የባለስልጣኑ የምርት ደህነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስናቀች አለሙ  በትምባሆን ምርት አደገኛነት  ላይ ያተኮረ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

በጽሑፋቸው ላይ እንዳሉት የሲጋራ ምርት ከ4 ሺህ እስከ 7 ሺህ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በመያዝ በሰዎች የተለያዩ የሰውነት የአካል ክፍሎች ላይ የካንሰር በሽታን ጨምሮ የልብ በሽታ፣የስንፈተ ወሲብ፣የአጥንት መሳሳትና መሳል በሽታዎችን ያስከትላል።

“ከጊዜ ወደ ጊዜ ስርጭቱን እያሰፋ የመጣውን የትምባሆ ምርትን ለመቆጣጠር ከአቅማችን በላይ አይደለም” ያሉት ዳይሬክተሯ  ስርጭቱን ለመቆጣጠር ጠንካራ ህግና ትምባሆን የሚጸየፍ ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ባለስልጣኑ  እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝና  የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የህዝብ ንቅናቄ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ክልል የመንግስትና ህዝብ ግንኙነት ቢሮ ተወካይ  አቶ ሰሎሞን ገብረ እግዚአብሔር ህጉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸራረፈ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

የህጉ  መሸራረፈ በክልሉ ተመዝግቦ የነበረውን ለውጥ ወደ ኋላ ሊመለስ ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩን ጠቁመው  ህብረተሰቡ ጀምሮት የነበረውን ጠንካራ የቁጥጥር ስራ አጠናክሮ ሊቀጥልበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በክልሉ  ጤና ቢሮ የጤና ቁጥጥር የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ባህረ ተካ በበኩላቸው በክልሉ ባለፉት ስድስት ዓመታት ትምባሆ ህዝብ በሚበዛባቸው ስፍራዎች እንዳይጨስ  ለመቆጣጠር የወጣውን ህግ  ተግባራዊ በማድረግ የተሻለ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህመ በመቀሌ፣ዓዲግራት፣ውቅሮና አክሱም ከተሞች ለውጥ መምጣቱን አመለክተው በሑመራ፣አላማጣና መኾኒ ደግሞ ለውጥ ያልታየባቸው ከተሞች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ክልሉ ቀደም ሲል ባስመዘገበው ውጤት ያገኘውን ዓለም አቀፍ ሽልማት ለማስጠበቅ አሁንም በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አቶ ባህረ ጠቁመዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ጋዜጠኞች  ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ ከ40 በላይ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን የጋራ ኮሚቴን በማዋቀር የተጀመረውን ስራ አጠናክሮ ለመሄድ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።