ፍርድ ቤቱ በኮሎኔል ካሳ ሮባ ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

81

አዲስ አበባ ታህሳስ 22/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮሎኔል ካሳ ሮባ ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

ኮሎኔል ካሳ ሮባ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችንና ሌሎች ንብረቶችን ሰብስቦ መልሶ መጠቀም መምሪያ ኃላፊ ለግዳጅ በደቡብ ሱዳን አብዬ ግዛት እንደነበሩ ይታወቃል።

ነገር ግን በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ በተላለፈው መሰረት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገዋል።

ተጠርጣሪው ኮሎኔል ካሳ ሮባ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመጠቀም በጥቅም በመመሳጠር ሌሎች ድርጅቶች ቁርጥራጭ ብረቶች ሰብስበው እንዲያቀርቡ በማድረግ፣ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸማቸውን ተገልጿል።

በመሆኑም ፖሊስ ከተለያዩ 46 የመንግስት መስሪያ ቤቶች መረጃ ለማሰባሰብና ሌሎች ከወንጀሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ላይ ምርመራዎችን ለማድረግ ተጨማሪ የ14 ቀናት ይፈቀድልኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪው ጠበቆች ኮሎኔል ካሳ በገዛ ፈቃዳቸው በውጭ አገራት ከተመደቡበት የሰላም አስከባሪ ኃይል መስሪያ ቤት መምጣቸውን ንጽሕናቸውን የሚያሳይ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።

ነገር ግን ተጠርጣሪው በከባድ የሙስና ወንጀል በመጠርጠራቸው የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ሲሉ ጠበቃቸው ያቀረቡትን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።

 የግራ ቀኝ ክርክሩን ሲያደምጥ የቆየው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ካቀረበው የ14 ቀናት ውስጥ 9 ቀኑን በመፍቀድ ለታሕሳስ 26 ቀን 2011ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም