በምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንዲፈታ የነቀምቴ ነዋሪዎች ጠየቁ

51

ነቀምቴ ታህሳስ 22/2011 በምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ  የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ ፡፡

በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ  ፓርቲና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር መካከል የተደረሰው ስምምነት በሥራ ላይ ባለመዋሉ በምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር  በሕዝቡ ውስጥ  ስጋት መፍጠሩን ነዋሪዎቹ ዛሬ በነቀምቴ ከተማ ባካሄዱት ውይይት ገልጸዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ፓስተር ተስፋዬ ኃይሌ እንዳሉት በሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የተደረሰው  ስምምነት  በአግባቡ  በሥራ ላይ ባለመዋሉ የተነሳ  ወደ ግጭት ተለውጦ በተለያዩ ቦታዎች የሰው ህይወት እየጠፋ ነው፡፡

በከተማው ስራ በመቆሙ ነግደው ቤተሰብ በሚያስዳድሩ እና በዕለት ገቢ ለሚተዳደሩ ወገኖች ላይ ከፍተኛ የኑሮ ጫና መፍጠሩንም አመልክተዋል፡፡

በመንግሥት ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁመው ሁለቱ የፖለቲካ  ድርጅቶች  በህብረተሰብ ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር በመገንዘብ በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት አስተካክለው የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡

" በሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የተፈጠው ግጭት ለሥልጣን   ከሆነ አሳፋሪና የኦሮሞን ሕዝብ አንገት ያስደፋ ነው፤ ለኦሮሞ ሕዝብ ልማት፣ዕድገትና ነፃነት ከሆነ ምንም የሚያጣላቸው ነገር የለም " ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ዶክተር ሞሲሳ ናቸው፡፡

በከተማው መንገድ ፣ሱቅ ፣ትምህርት ቤት የሚዘጉ ክፍሎችም ቆም ብለው በሀገሪቱ ላይ የሚያከትለውን ችግር በማየት የተገኘውን ለውጥ ለማስቀጠል መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

ሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች አሁን በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ እንዲፈቱም ጠይቀዋል፡፡

የምሥራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ በቀለ በበኩላቸው ሰላም ከሌለ ወጥቶ መግባትና ፣ሰርቶ መኖር እንዳማይቻል ገልጸዋል፡፡

ሰላምን ለማስፈን ደግሞ የሁሉም የህብረተሰቡ ክፍል ድርሻ በመሆኑ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም  አሳስበዋል፡፡

"የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የአንድ አባት ልጆች በመሆናቸው እርስ በርስ መወጋት የለባቸውም " ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ፖሊስ  ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር  ጀኔራል ረታ በላቸው ናቸው፡፡

መንግሥት በውይይት እንጂ በግጭት እንደማያመን ያመለከቱት ምክትል ኮሚሽነሩ ኦነግ በአስመራ ለውጡን ለማስቀጠል  የገባውን ቃል በማክበር ወደ ሰላማዊ ውይይት መምጣት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በአካባቢው ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በተካሄደው ውይይት የኃይማኖት አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣የመንግሥት ሠራተኞችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም