በሶማሌ ክልል የመጠጥ ውሃ እጥረት አጋጥሟል

84

ጂግጂጋ/መቱ ታህሳስ 22/2011 ባጋጠማቸው የመጠጥ ውሃ እጥረት ለችግር መጋለጣቸውን በሶማሌ ክልል አፍዴርና ቆረሃይ ዞኖች  አርብቶ አደሮች  ገለጹ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቦር ዞን ቃሮ ከተማ ተመሳሳይ ችግር እንዳለ ተመልክቷል፡፡

በሶማሌ ክልል   ቆረሃይ ዞን ጎግሎ ወረዳ ኢስሞደይ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዴቅ መሀሙድ ለኢዜአ እንዳሉት በአካባቢያቸው የዝናብ ውሃን በባህላዊ መንገድ  በማሰባሰብ ለሰውና ለእንስሳት የመጠጥ ውሃ ሲጠቀሙ ቆይተዋል፡፡

ሆኖም  ባለፈው ጥቅምትና ህዳር ወራት የጠበቁት  ዝናብ አነስተኛ በመሆኑ የሚያሰባሰቡበት ኩሬ  ውሃ እንዳልያዘ ጠቁመው በዚህ ምክንያት ለችግር መጋለጣቸውና  አስቸኳይ የውሃ አቅርቦት ከመንግስት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

በወረዳው የውሃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሐሰን አህመድ በበኩላቸው በወረዳው በሪጭስላይ፣እስሞደይ፣ሙቅዴርና ገሪዳ-ሂደን የተባሉ አርብቶ አደር ቀበሌዎች የውሃ ችግር ማጋጠሙን ገልጸዋል፡፡

የቀበሌዎቹ ነዋሪ  አርብቶ አደር በአርባ ኪሎ ሜትር ርቀት ከሚገኘው  ቀብሪ ደሃር አካባቢ  በቦቴ ውሃ ለማመላለስ ለክልሉ የቦቴ  አቅርቦት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

በአፍዴር ዞን ጎድጎድ ወረዳ አርብቶ አደር አቶ ኢብራሂን ሼህ መሀመድ በአካባቢያቸው በቂ ዝናብ ባለመጣሉ ቀደም ብለው በባህላዊ መንገድ ያሰባሰቡት ውሃ  እያለቀ እጥረት እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት  የራሳቸውንና የሚያረቧቸውን  የቤት እንስሳት የመጠጥ ውሃ  አጥተው  ከአካባቢቸው ርቆ ወደ ሚገኘው   ዋይብ ወንዝ ድረስ በመጓዝ ለመጠቀም መገደዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ የቅደመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ የስራ ሂደት ተወካይ አቶ ዩሱፍ ኢስማን በክልሉ ምስራቃዊ ዞኖች በተያዘው ዓመት የተጠበቀው ዝናብ በበቂ ሁኔታ ባለመጣሉ ምክንያት የሰውና የእንስሳት የመጠጥ ውሃ እጥረት ማጋጠሙን ገልጸዋል፡፡  

በቅርቡ የክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ አስተባባሪነት ከተለያዩ ሴክተር ቢሮዎችና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች ባደረጉት ዳስሳ ጥናት ችግሩ ያጋጣማቸው ቀበሌዎች ተለይቷል፡፡

አቶ ዩሱፍ እንዳሉት በጥናቱ መሰረት በክልሉ 150  የአርብቶ አደር ቀበሌዎች አስቸኳይ የውሃ አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸው  ታውቋል፡፡

እስካሁን ችግሩ ጎልቶ በሚታየይባቸው ሃምሳ ሰባት ቀበሌዎች  ተሸከርካሪ ቦቴዎችን ማሰማራታቸውን አመልክተዋል፡፡

" 16 ቦቴዎች ደግሞ በጥገና ላይ ናቸው፤ ቀሪዎቹ  መንግስትና  መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች እንዲሸፈን ጥያቄ አቅርበናል"ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል  ደግሞ በኢሉአባቦር ዞን በቢሎ ኖጳ ወረዳ ቃሮ ከተማ  የተገነባው የውሀ ተቋም ተገቢውን አገልግሎት እየሰጣቸው እንዳልሆነ  አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አንዋር ሸሪፍ  ለኢዜአ  እንደተናገሩት የተገነባው  የውሀው ተቋም ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ ባለመሆኑ ንጽህናውን ያልጠበቀ የወንዝ ለመጠቀም ተገደዋል፡፡

" የውሀ ተቋሙ ግንባታው ሲጠናቀቅ ደስታ ተሰምቶን ነበር" ያሉት አቶ አንዋር እስካሁን ችግሩን ባለመፈታቱ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ ፋንታዬ ፈይሳ የተባሉት የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው የውሀ ፕሮጄክቱ ግንባታ ሲከናወን ድጋፍ በመስጠት መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ሆኖም ከተጠናቀቀ በኋላ  አገልግሎት ባለመስጠቱ ንጽህናው ያልተጠበቀ ወንዝ ለመጠጥ በመጠቀም ለበሽታ  መጋለጣቸውን  አስረድተዋል፡፡

መንግስት የገጠማቸውን ችግር ተረድቶ አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባም  አመልክተዋል፡፡

የዞኑ ውሀ ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጅሬኛ ዱፌራ የከተማውን የንጹህ ውሀ ችግር ለማቃለል ከዓመት በፊት የተጠናቀቀው  የውሀ ፕሮጄክት ከከተማው የመሬት አቀማመጥ የተነሳ ውሀ በተሟላ ሁኔታ  እንደማያመርት ተናግረዋል፡፡

" ከከተማው የመሬት አቀማመጥ ጋር ተደምሮ  ለከተማው የሚቀርበው ውሀም ራቅ ካለ አካባቢ ስለሚሳብ ለነዋሪው ማዳረስ አልተቻለም " ብለዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታትም የዋና ውሀ መሳቢያ መስመር ከስምንት ኪሎሜትር ወደ አምስት ኪሎሜትር የሚቀንስ አዲስ ዲዛይን ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱንና  ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም