የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት የግንቦት 20ን የድል በዓል አከበሩ

125
ድሬዳዋ ግንቦት 17/2010 የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሙሁራንና ተማሪዎች በተሰማሩበት መስክ ኃላፊነታቸውን ጠንክረው በመወጣት ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የተመዘገቡ የልማት ውጤቶችን ሊያስቀጥሉ እንደሚገባ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አሳሰቡ። የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ 27ኛውን የግንቦት 20 የድል በዓል ዛሬ በፓናል ውይይት አክብረዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ እንደገለጹት ድሉ የአገሪቱ ህዝቦች ማንነታቸው እንዲከበር፣ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲገነቡና ህገ-መንግስታዊ ዋስትና እንዲጎናጸፉ መሠረት የተጣለበት ነው፡፡ ድሉን ተከትሎ በመላው ሀገሪቱ ከትምህርት በተጨማሪ ዘርፈ ብዙ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ከህዝቡ በስፋት እየቀረበ ለሚገኘው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መንግስት ምላሽ ለመስጠት ርብርብ እያደረ ባለበት ወቅት ዩኒቨርሲቲው ሙሁራንና ማህበረሰብ በተሰማሩበት መስክ ውጤት በማስመዝገብ የለውጡ አጋር መሆን እንዳለባቸው መክረዋል። የነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎችም ለሀገሪቱ ዕድገትና ሰላም ከወዲሁ የድርሻቸውን በመወጣት በግንቦት ሃያ የተገኘውን የድል ውጤት የማስቀጠል ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው መምህር ብርሃኑ ኮንቱ በበኩሉ የግንቦት 20 ድል በሀገሪቱ በሁሉም መስክ ለውጥ እንዲመጣ በር መክፈቱን ጠቁሞ፣ በተለይ አሁን በመላው ሀገሪቱ እየተፈጠረ የሚገኘውን የመነቃቃት ተስፋ መንግስት በመጠቀም ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ በመስራት የድሉን ውጤት እንዲያጠናክር ጠይቋል። "በቅርቡ የተፈጠረው የአመራር ለውጥና ለውጡን ተከትሎ የሚታየው መነቃቃት በቀጣይ የአገሪቱን የልማት ውጤቶች ይበልጥ ፍሬያማ እንዲሆኑ ያግዛል" ያለው ደግሞ የሦስተኛ ዓመት የህግ ተማሪ አብዱላሂ ቁታ ነው፡፡ "የላቀ ብሔራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለላቀ ሀገራዊ ስኬት" በሚል መሪ ሀሳብ በተከበረው በዓል ላይ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ሥርዓት ዋና ዋና ስኬቶችን የሚገልጽ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በውይይቱ ላይም ፌደራላዊ ሥርዓቱ ራስን በራስ ለማስተዳደር፣ የሀገሪቱን አንድነት ለመጠበቅ፣ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ ማህበራዊና ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም