የመንገድ ፈንድና መንገድ ኤጀንሲዎች በመንገድ ሀብት አጠቃቀምና ጥገናዎች ዙሪያ ሊያሰራ የሚችል አዲስ ውል ተፈራረሙ

79

አዲስ አበባ ታህሳስ 22/2011 የመንገድ ፈንድና የክልሎች የመንገድ ኤጀንሲዎች በመንገድ ሀብት አጠቃቀምና ጥገናዎች ዙሪያ ሊያሰራ የሚችል አዲስ ውል ተፈራረሙ።

ውሉ በጀት የተመደበላቸው የመንገዶች ባለስልጣናትና ኤጀንሲዎች በጀታቸውን በአግባቡ እየተጠቀሙበት ስለመሆኑ የሚከታተልና ከብክነት ነጻ በሆነ መልኩ የሚያሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የመንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች ከተወከሉ የመንገድ ባለስልጣናትና ኤጄንሲዎች ጋር ያደረገው ይህ ውል የመንገድ ሀብት አጠቃቀምን ተገቢነት ለመቆጣጠር የሚያስችል የተሻለ አሰራር ለመዘርጋት ነው፡፡

በመድረኩ በመንድ ጥገናና የመንገድ ሃብት አጠቃቀም ዙሪያ ውይይት የተደረገ ሲሆን በተለይ ክልሎችን ወክለው የመጡ ተሳታፊዎች ባነሱት ሃሳብ መንገዶችን መልሶ የመጠገን ሂደት ላይ ትኩረት እየተሰጠበት እንዳልሆነና የሚመደብላቸው በጀትም አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ኤጀንሲዎቹን ወክለው የመጡ ተሳታፊዎች እንደገለጹት ከሆነ በጀት በወቅቱ ባለመለቀቁ የጥገና ሂደቱ ላይ የጥራት ችግር እየፈጠረባቸው እንደሆነም ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታከለ ጌታቸው በሰጡት አስተያየት፣  በዚህ ዓመት በወቅታዊና በመደበኛ የምንጠግነው መንገዶች ከ3 ሺህ 400 ኪሎ ሜትር በላይ ሲሆን የተያዘው በጀት ደግሞ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ነው።

በዚህም አሁን ባለው የማሽን፣ የሰው ሃብትና የነዳጅ ሁኔታ እንዴት የታሰበው ጥራት ተጠብቆ  ሊሰራ ይችላል በማለት ይጠይቃሉ።

የኦሮሚያ መንገዶች ባለሰልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢታፋ በበኩላቸው፣ ኦሮሚያ ወሰጥ ያሉት መንገዶች ለሌሎች አጎራባች ክልሎችና ከተሞች ተመጋጋቢ መንገዶቸ ናቸው።

መንገዶቹ በርካታ ተሽከርካሪዎችን በቀን ስለሚያስተናግዱም በየጊዜው ጥገናን ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን በታሰበው ልክና መጠን በጥራት ለመጠገን በቂ የሆነ ፈንድ ባለመኖሩ መንገዶቹ አንድ ክረምት ሳያሻግሩ ይበላሻሉ ብለዋል።

የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መብት አድማሱ እንደሚሉት ደግሞ፣ "በእኛ አካባቢ የመንገድ ጥገና ሊደረግ ሲል ትልቅ ችግር ሆኖ ያለው የማሽነሪ ችግር ነው፤ ስራውን በአግባቡ እንዳንሰራም ማነቆ ሆኖብናል" ብለዋል።

ክልሎቹን ወክለው የመጡት የመንገድ ኤጀንሲዎች በአብዛኛው ያነሱት ችግር የሚመደብላቸው በጀት አነስተኛ በመሆኑ የመንገድ ጥገናዎቹን በአግባቡና በጥራት ለማካሄድ መቸገራቸውን ነው።

ዘመናዊ የመንገድ ጥገናና ግንባታ ለማድረግም፣ ዘመናዊ የሆኑ ማሽነሪዎች፣ በቂ የሰው ሃይልና ክትትል ያስፈልጋል ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ።

መንገዶችን መልሶ ከመጠገን ይልቅ መንግስት አዳዲስ መንገዶችን መገንባት ላይ ትኩረት እያደረገ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ያሉንን መንገዶች በአግባቡና በወቅቱ እንዲጠገኑ የመንገድ ፈንዱ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የመንገድ ፈንድ ዕህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ረሺድ መሃመድ በቂ በጀት እየተመደበ አይደለም ለሚለው በአገሪቷ በዓመት ጥገና ለማድረግ በከፍተኛው 7 ቢሊዮን በዝቅተኛው ደግሞ 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ይገባል።

ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ እየተሰበሰበ ያለው 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በመሆኑ በበጀቱ 50 በመቶውን ብቻ እየሸፈንን ነው ብለዋል።

በመሆኑም ባለው በጀት በማብቃቃት መጠቀም ያለንን የመንገድ ሀብት የቱ ጥገና ያስፈልገዋል? የቱስ ይዘግይ? የሚለውን ለይቶ በማውጣት በሃላፊነት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ማሺነሪ በተመለከተም ጥያቄዎቹን በመቀበል ምላሽ አንደሚሰጡበት ገልጸው፣ አሁን እየተሰራበት ያለው አሰራር ከ5 ዓመትና 6 ዓመት በፊት

እየተሰራበት የመጣ በመሆኑ መከለስና መስተካከል የሚገባቸው አሰራሮች እንደሚስተካከሉ አክለዋል።

የተፈራረሙት ውልም በዋናነት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንን ጨምሮ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች መንገዶች ባለስልጣናትና ኤጀንሲዎች በሚሰሩት አጠቃላይ የመንገድ ጥገና ዙሪያ የበጀት አጠቃቀምንና የስራ ሁኔታን መከታተልን ያለመ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም