በኢትዮጵያ ቮሊቦል ታሪክ በአንድ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከፍተኛ ነጥብ ተመዘገበ

932

አዲስ አበባ ታሀሳስ 22/2011 በ2011 ዓ.ም ሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሙገር ሲሚንቶና ወላይታ ድቻ ባደረጉት ጨዋታ በኢትዮጵያ ቮሊቦል ታሪክ በአንድ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከፍተኛ ነጥብ ተመዝግቦበታል።

አራተኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ትናንት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተካሂደዋል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ሙገር ሲሚንቶና ወላይታ ድቻ ባደረጉት ጨዋታ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወላይታ ድቻ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወላይታ ድቻ ሙገርን 42 ለ 40 ያሸነፈበት ነጥብ በኢትዮጵያ የቮሊቦል ታሪክ በአንድ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከፍተኛ ነጥብ የተመዘገበበት ሆኗል።

ጨዋታው ከ2 ሰዓት በላይ የፈጀና ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር የተገኘበትም ነበር።

ውጤቱን ተከትሎ የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ወላይታ ድቻ ሶስተኛ ጨዋታውን ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በአንጻሩ ሙገር ሲሚንቶ ከሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች አሸናፊነት በኋላ በሊጉ የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናግዷል።

ሁለቱ ክለቦች በዘንድሮው የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጠንካራ አቋም እያሳዩ ይገኛሉ።

በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ መከላከያ በሦስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጣና ባህር ዳርን 3 ለ 0 በማሸነፍ በሊጉ ሦስተኛ ድሉን አስመዝግቧል።

መከላከያ ከዚህ በፊት ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ፌደራል ማረሚያ ቤቶችንና አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽን ማሸነፉ ይታወሳል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም በተደረገው ሌላ ጨዋታ አዲስ አበባ ፖሊስ ፌደራል ማረሚያ ቤቶችን በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 አሸንፏል።

በክልል ከተማ ሮቤ ላይ መዳ ወላቡ ዩኒቨርስቲ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መከላከያን 3 ለ 1 ያሸነፈ ሲሆን መከላከያ በሊጉ የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናግዷል።

ባህርዳር ላይ ጣና ባህርዳር አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽን በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 ረቷል።

በፕሪሚየር ሊጉ አዲስ ተሳታፊ የሆነው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ እስካሁን ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

ስምንት ክለቦች በሚሳተፉበት የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ  ስድስቱ ክለቦች ሁሉንም ጨዋታቸውን አድርገዋል።

በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ሶዶ ላይ ወላይታ ዲቻ ከ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ አዲስ ተሳታፊው በአዲስ አበባና ውሃ ፍሳሽ ጥያቄ አቅራቢነት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ የሚታወስ ነው።

በዚሁ መሰረት የሁለቱ ጨዋታ በተስተካካይ መርሃ ግብር የተያዘ ሲሆን ጨዋታው የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን በቀጣይ በሚያሳውቀው ጊዜ የሚካሄድ ይሆናል።

አምስተኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የሚካሄዱ ይሆናሉ።

የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊጉ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኝ ውድድር ነው።